አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተጠናቀቁና በሂደት ላይ ባሉ 131 ምርምሮች ዙሪያ ከየካቲት 26-28/2010 ዓ/ም ዓመታዊ ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደገለጹት ዓውደ ጥናቱ የተዘጋጀበት ዓላማ በሂደት ላይ ያሉና ተሠርተው የተጠናቀቁ የምርምር ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ ፈትሾ ገንቢ አስተያየቶችን በማሰባሰብ የምርምር ሥራዎች የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ማድረግ ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው 194 የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን የምርምር ሥራዎቹን በማስተቸትና በማስገምገም ደረጃቸውን ጠብቀው በታዋቂ ዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ እንዲታተሙ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የምርምር ግኝቶች የህብረተሰቡን ችግር እንዲፈቱ ለማስቻል የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አካል ሆነው ፕሮጀክት ይቀረጽላቸዋል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው ይህ መድረክ የምርምሮቹን ደካማና ጠንካራ ጎን በመለየት ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ያስችላል ብለዋል፡፡ በተመራማሪዎች መካከል፣ በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና በባለድርሻ አካላት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲውና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ስኬታማ ምርምሮችን ለመሥራት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት በዩኒቨርሲቲው የሚሠሩ ምርምሮች በዋናነት የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ በተለያየ ደረጃ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዩኒቨርሲቲው በውኃ ሀብት ልማትና አስተዳደር፣ በብዝሃ ህይወትና የባህል ብዝሃነት፣ በተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች እንዲሁም በቢዝነስ ሀሳቦች ፈጠራና ልማት ምርምሮችን በማድረግ ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለመሸጋገር እየሠራ ይገኛል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች መካከል ‹‹socio-cultural and institutional factors affecting gender mainstreaming>> በሚል ርዕስ በመ/ር ሎምቤቦ ታገሰ የቀረበው አንዱ ነው፡፡ በጥናቱ የሴቶች የት/ት ደረጃ፣ በሴቶች ት/ት ላይ ያለው አመለካከት፣ ኃላፊነትን ለመሸከም የሴቶች ፈቃደኛ አለመሆን፣ በሴቶች አቅም ዙሪያ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶች እና ወንዶች ሴቶች አመራር እንዲሆኑ አለመፈለጋቸው እንደ ተግዳሮት ቀርበዋል፡፡ ለዚህም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለህበረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው በጥናቱ እንደ መፍትሔ ተጠቁሟል፡፡

ሌላኛው ጥናታዊ ጽሁፍ ‹‹Quality Characteristics and the Relation with Flowering in Sugarcane in Ethiopia>> በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር A. Q. Khan የቀረበ ሲሆን ጥናቱ ለሀገራችን የአየር ንብረትና መሬት ተስማሚ እንዲሁም ጥራት ያላቸውና ምርታማ የሆኑ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎችን መለየትን ዓላማ አድርጎ የተሠራ ነው፡፡ ለምርምር ሥራው 16 የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ተተክለው ተስማሚ የሆኑት መለየታቸውን ተመራማሪው ገልፀዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የሶሥት ቀናት ውሎ በምርትና ምርታማነት፣ በህፃናት ጤናና የተመጣጠነ ምግብ፣ በእናቶች ጤናና HIV/AIDS፣ በውኃ ብክለትና ከፋብሪካዎች የሚወጡ ተረፈ ምርቶች፣ በልማዳዊ ሥርዓትና ተረኮች እና በቱሪዝም ኢንደስትሪ የአስጎብኚ ጥራት ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባችዋል፡፡

በመድረኩ የዩኒቨርሲተው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራን፣ ደቡብ ክልል ከሚገኙ 5 ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ የምርምር ዳይሬክቶሬት ኃላፊዎች፣ ከዞን ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት መምሪያ እና ከአ/ምንጭ ግብርና  ምርምር ማዕከል የተወጣጡ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡