9ኛው ዙር የሥነ-ሕንፃና ከተማ ፕላን ተማሪዎች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የካቲት 24/2010 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በሚገኘው አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

ከ37 ተመራቂ ተማሪዎች መካከል 29ኙ ወንዶች ሲሆኑ 8ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ተማሪ በእምነት ካሣዬ 3.71 በማምጣት 1ኛ፣ ተማሪ ኢዩኤል ተስፋዬ 3.36 በማምጣት 2ኛ እና ተማሪ ምንተስኖት ካሣሁን 3.30 በማምጣት ሦስተኛ ሆነው ተሸልመዋል፡፡ ተማሪ ፍሬዘር ንጉሤ 3.12 በማምጣት ከሴት ተመራቂዎች በአንደኝነት ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ሀብት ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ቦርድ አባልና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ገረመው ሣህሉ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት የሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን ባለሙያዎች ከሌሎች ተጓዳኝ ሙያዎች ጋር ከዕቅድ ጀምሮ ሙያዊ ወሰንን ባልተጋፋ መልኩ ተባብረው ከሠሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ምሩቃን በሙያዊ ሥነ-ምግባር ታንፃችሁ በየጊዜው በትምህርትና ስልጠና ራሳችሁን በማሻሻል በጋራ ለመሥራት መዘጋጀት ይኖርባችኋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው መንግስት የሀገሪቱን ከተሞች ለህዝቡ ፅዱና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየሠራ በሚገኝበት በዚህ ወቅት መመረቃችሁ በዘርፉ እየተካሄደ የሚገኘውን ልማት ለማሳደግ ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ምሩቃን ያጠናቀቁት ይህ የትምህርት ምዕራፍ የመጨረሻ አለመሆኑን ጠቅሰው ከዩኒቨርሲቲው የገበዩትን ዕውቀት ከነባራዊው የሥራ ዓለም ከሚያካብቱት ልምድ ጋር በማዋሃድ ብቁ ባለሙያ ለመሆን እንዲጥሩ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ተወካይና የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳ አርክቴክት ዘርዓይ መስፍን በመልዕክታቸው ‹‹ወደ መስኩ ስትገቡ መንታ መንገድ ላይ ቆማችሁ ራሳችሁን ታገኛላችሁ፤ አንደኛው ወደ እውነተኛ ስኬት የሚያደርስ ትክክለኛ መንገድ ሲሆን ሁለተኛው ወደ ስኬት የሚያደርስ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡ አቋራጩ መንገድ ለሀገሪቱ ዕድገት ማበርከት የሚገባንን ሳናበረክት ህብረተሰባችንን ጨቁነን የምንበለፅግበት መንገድ በመሆኑ በፍፁም ሳትሠሩ የምታገኙበትን መንገድ አትምረጡ፤ እንደ የችሎታችሁ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ ካደረጋችሁ እውነተኛ አምላክ የሚገባችሁን ሽልማት ዋጋ እንደሚሰጣችሁ እርግጠኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡

ተማሪ በእምነት ካሳዬ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ በሙያው ልምድ ያላቸው መምህራንና እንግዶችን በመጋበዝ እና ዓውደ-ጥናት በማዘጋጀት በቂ እውቀት እንድንጨብጥ አድርጎናል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ተማሪ ፍሬዘር ንጉሤ በበኩሏ የመማሪያ ግብዓቶች መሟላት ስኬታማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የሚረዳ መሆኑን ገልፃ ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ያስገነባው የትምህርት ክፍሉ የዲዛይን ስቱዲዮ የመማር ማስተማር ሂደቱን ምቹ አድርጎ ተወዳዳሪ እንድንሆን አግዞናል ብላለች፡፡

የተመራቂ ተማሪዎች ተወካይ ተማሪ እንዳለ ሙሉጌታ በአስተያየቱ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያስተዋላቸውን የተለያዩ ህንፃዎች ግንባታ፣ የግቢ ውበት ሥራዎች እና መሰል በጎ ለውጦችን አውስቷል፡፡ የሥነ-ሕንፃና ከተማ ፕላን ትምህርት በባህሪው እርስ በርስ መግባባትን የሚፈልግ በመሆኑ ተማሪዎች እርስ በእርሳቸው መተጋገዝ እንዲችሉ በአንድ የመኖሪያ አካባቢ እንዲኖሩ ቢደረግ እና በተማሪዎችና መምህራን መካከል የሚፈጠሩ ያለመናበብ ችግሮች የተማሪውን የመማር ተነሳሽነት የሚቀንሱ በመሆኑ መልካም ተግባቦት እንዲኖር ቢሠራ ተማሪዎች በሁሉም ኮርሶች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ለት/ክፍሉ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት እና የውይይት መድረኮችንና ሴሚናሮችን ማዘጋጀት እንደ ተማሪ ማድረግ ስንችል በተለያዩ ምክንያቶች ሳይከናወኑ ከቀሩ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው ያለው ተማሪ እንዳለ ስለሆነም ከእነርሱ የሚቀጥሉ ተማሪዎች በዚህ ረገድ ጠንክረው እንዲሠሩ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ባሳለፉት የትምህርት ዓመታት ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ላበረከተው መልካም ነገር በተመራቂ ተማሪዎች ስም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የ9ኛ ዙር ተመራቂዎች 5½ ዓመት ቆይታ በማድረግ የመጨረሻው ባች ሲሆኑ ከዚህ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ የሥነ-ሕንፃና ከተማ ፕላን ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በ5 ዓመት የሚመረቁ ይሆናል፡፡