ዩኒቨርሲቲው ለከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች፣ በዜጎች ቻርተር፣ በለውጥ መሣሪያዎች ትስስር፣ በህዝብ ክንፍ ተሳትፎ ግንባታ እና በመንግሥት ሠራተኞች የሥነ-ምግባር ኮድ ዙሪያ ከመጋቢት 7-8/2010 ዓ.ም የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የስልጠናው ዓላማ ለዩኒቨርሲቲው አመራር በአዳዲስ አሠራሮች ዙሪያ ግንዛቤ በማስጨበጥ የአመራሩን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ማዳበር ነው፡፡ በተጨማሪም በእያንዳንዱ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ሠራተኞች የሚያጋጥሟቸውን ክፍተቶች በመሙላት ውጤታማ ተግባር እንዲፈጽሙ ይረዳል፡፡

በስልጠና መድረኩ የስብሰባ አተገባበር መመሪያ እና የመንግሥት ሠራተኞች ሥነ-ምግባር ኮድ ሰነዶችን ያቀረቡት የሰው ሀብት አስ/ር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ እንደተናገሩት ስብሰባ በዕለት ተዕለት ሥራችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት፣ ውሳኔዎችን ለመወሰን፣ በተለያዩ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስና ወሳኝ መረጃዎችን  ለማስተላለፍ  በጋራ የምንመክርበት መሣሪያ ነው፡፡ በመሆኑም ውጤታማና ቀልጣፋ ስብሰባ ለማካሄድ በቅድመ ስብሰባ፣ በስብስባ ወቅትና በድህረ ስብሰባ መደረግ የሚገባቸው ጉዳዮች በትክክል መተግበራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ሠራተኞች የሚመሩበት የሥነ-ምግባር መርሆዎችን ሥራ ላይ ማዋል ሠራተኞች የተጣለባቸውን ሀገራዊና ህዝባዊ አደራን በብቃት፣ በታማኝነትና በውጤታማነት እንዲፈጽሙ ያስችላል፡፡

በውጤት ተኮር ሥርዓት አተገባበርና በዜጎች ቻርተር ዙሪያ ሰነዶችን ያቀረቡት የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ እንደተናገሩት ስኬታማ የውጤት ተኮር አተገባበር ሥርዓት ሊረጋገጥ የሚችለው የበላይ አመራሩ በባለቤትነት አቀናጅቶና አስተሳስሮ መምራት ሲችል እና ጠንካራ የተግባቦት ሥርዓትና ውጤትን መሠረት ያደረገ ማበረታቻ ሲኖር ነው፡፡ በተጨማሪም የተጠያቂነት፣ የግልጸኝነት፣ የፍትሃዊነትና የህግ የበላይነት መርሆዎችን ተግባራዊ በማድረግ ከዜጎች ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጣን፣ ውጤታማና ቀልጣፋ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች፣ በለውጥ መሣሪያዎች ትስስርና በህዝብ ተሳትፎ ግንባታ ሰነዶች ላይ ገለፃ ያደረጉት የተቋማዊ ለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ በፈቃዱ እንዳብራሩት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከአመራሩ ቁርጠኝነት፣ አሳታፊነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልጸኝነት ታማኝነት እና ወቅታዊ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅ ሲሆን ከሠራተኛው ደግሞ መልካም ሥነ-ምግባር፣ የአገልግሎት ጥራት፣ ደንበኛን ማክበርና ታማኝነት ይጠበቃል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ መልካም አስተዳደር ሲረጋገጥ የለውጥ መሣሪያዎች ትስስር ግቡን የሚመታ ሲሆን ውጤታማነት ይጨምራል፡፡

ከተሳታፊዎች በቀረቡ አስተያየቶችና ጥያቄዎች መሠረት የጋራ ውይይት ተካሂዶ ከአሰልጣኞችና ከፕሬዝደንቱ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ በስልጠናው የኮሌጅ ዲኖች፣ የት/ቤት ኃላፊዎች፣ የትምህርት ክፍል ተጠሪዎችና አስተባባሪዎች፣ ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው ግንዛቤ የሚያስጨብጥና ወደ ተግባር ወርደው ለሚሠሩት ሥራ አጋዥ እንደሚሆን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡