በ ECDD (Ethiopian Center for Disability and Development) እና አይሪሽ-ኤይድ ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ትብብር ለዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ እና የአስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ለትምህርት ክፍል ኃላፊዎች በአካቶና ልዩ ፍላጎት ትምህርት ላይ መጋቢት 10/2010 ዓ/ም የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በ ECDD የደቡብ ሪጅን ኢንክሉሲቭ ላይቭሊሁድ አስተባበሪ (inclusive livelihood coordinator) ወ/ሪት አሚ ጋንታ እንደገለጹት በአካል ጉዳተኞች ሜይንስትሪሚንግ ፕሮግራም በኩል የተሰጠው ስልጠና በተቋሙ በርካታ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለማስተናገድና ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ ምቹ የሥራና የትምህርት አካባቢን ከማጎልበት አንጻር ባሉ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ በማስረጽ ለማሻሻልና እንደ አገር ተሳትፏቸውን ለማሳደግም ይረዳል፡፡

ስልጠናው ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንጻር ጉልህ ድርሻ ያለውና በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የአመራሩን ግንዛቤ ማሳደግ በተማሪዎች ብሎም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የአመለካከት ውስንነት በመቅረፍ ተሳትፎው እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የልዩ ፍላጎት ባለሙያ አቶ አሊ ሳኒ ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት ገልፀዋል፡፡

ECDD ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር ለአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ እድገት አቅም በመፍጠርና ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ድጋፍ በመስጠት ውጤታቸውንና ተሳትፏቸውን ለማሻሻል የሚሠራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ ማዕከሉ የአካል ጉዳተኞች አጠቃላይ ጤና፣ ትምህርት፣ አኗኗር እና የማህበረሰብ ለውጥ ላይ እየሠራ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተፈጠረው ትብብር አካል ጉዳተኞች በራስ የመተማመን አቅም ኖሯቸው በትምህርት፣ በሥራ እና በአመራርነት ውጤታማ እንዲሆኑ ስልጠናና ሌሎችም ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛል፡፡