የዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ ከሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ስፖርት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዞኑ ለሚገኙ 52  አሰልጣኞች የእግር ኳስና የአትሌቲክስ የጀማሪ አሰልጣኝነት ስልጠና ከመጋቢት 14/2010 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት በኮንሶ ካራት ከተማ ሰጥቷል፡፡ ስልጠናው የተሰጠው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች በተመደቡ አሰልጣኞች ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ስፖርት አካዳሚ በበጀት ዓመቱ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል ለስፖርት ባለሙያዎች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና መስጠት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት የአካዳሚው ዳይሬክተር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው ዕቅዱን ለማሳካት በተለያዩ ጊዜያት በጋሞ ጎፋ ዞን ለሚገኙ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ይህ ስልጠናም በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ጥያቄ መሰረት በአትሌቲክስና በእግር ኳስ የመጀመሪያ ደረጃ አሰልጣኝነት ባለሙያዎችን ለማብቃትና በሀገሪቱ ስፖርት ተሳታፊ ወጣቶችን ለማፍራት ታልሞ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች አትሌቲክስንና እግር ኳስን በሀገር ደረጃ ይበልጥ ለማስፋፋት ከስር/grass root level/ በመነሳት መሥራት ተገቢ መሆኑን በማመን ከክልሎች፣ ከዞኖችና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀናጅተው በመስራት ላይ እንደሚገኙ አሰልጣኞቹ አቶ ሰይፉ ዓለሙ እና አቶ አይቸው አባይ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት ከትምህርት ቤት ለተወጣጡና የፕሮጀክት ወጣቶችን በማሰልጠን ላይ ላሉ እና በዘርፉ ለሚሳተፉ አካላት የ1ኛ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት በራስ መተማመን እንዲኖራቸውና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚያግዝ እንዲሁም በሀገር ደረጃ ተተኪ ለማፍራት የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

አሰልጣኝነት የተለያዩ ችግሮችን ማለፍና ትዕግስት የሚጠይቅ፣ ከልብ የሆነ ተነሳሽነት የሚያስፈልገው እና በአንድ ጀምበር ሳይሆን በሂደት ውጤት የሚገኝበት ሙያ መሆኑን ተረድተው ሰልጣኞች ያገኙትን ክህሎት በስራቸው ላሉ ህፃናትና ወጣቶች በተገቢው መልኩ በማውረድ ለሀገራቸው ብቁ ዜጋ ለማፍራት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሰልጣኝ አቶ ሰይፉ አለሙ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ም/ኃላፊና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኮሬ ዱባለ ዞኑ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ስልጠናውን በማዘጋጀቱ በዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ስም ምስጋናቸውን አቅርበው ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸውን ዕድልና ምቹ አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ሰልጣኞች በስፖርቱ ዙሪያ ለዞኑ የተቻላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ዞኑ ለዩኒቨርሲቲው የተለያዩና ሰፊ ጥያቄዎችን ቢያቀርብም ይህ የመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኝነት ስልጠና እንደ ጅምር የሚታይና ለወደፊቱም በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የሚሰጡ መሆኑን በአካዳሚው የክህሎት ስልጠና ማዕከል ተጠሪ አቶ በዛብህ አማረ ተናግረዋል፡፡ ዞኑ በዘርፉ ለሀገሪቱ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት በሚያደርገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው ምንጊዜም ከጎኑ የሚቆም መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ስልጠና ቡድን መሪ አቶ አንተነህ ጌቱ በበኩላቸው ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ የተሰጠው ይህ ስልጠና በዞኑና በወረዳዎች ውስጥ ታዳጊ ወጣቶችንና ፕሮጀክቶችን በማሰልጠን ላይ ያሉ አማተር አሰልጣኞችን አቅም የሚገነባ ከመሆኑም ባሻገር በዞኑ ለሚገኙት የኮንሶ ኒው ዮርክ እግር ኳስ ክለብና ዶሃ አትሌቲክስ ክለብ ተተኪ ስፖርተኞችንና አሰልጣኞችን ለማፍራት ይረዳል ብለዋል፡፡