ዩኒቨርሲቲው የ2010 ዓ/ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማውን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላት በተገኙበት ሚያዝያ 10/2010 ዓ/ም አከናውኗል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት ግምገማው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በሁሉም ዘርፎች የታቀዱ ተግባራት አፈፃፀማቸውን በመፈተሽ ዝቅተኛ አፈፃፀም በታየባቸው መስኮች በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ በማድረግ በመማር ማስተማርም ሆነ በሌሎች የዩኒቨርሲቲው አበይት ተልዕኮዎች ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ ይረዳል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ግ/ዳይ/ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ ባቀረቡት ሪፖርት አንደተመለከተው የት/ት አግባብነትና ጥራትን ለማሳደግ ኮርሶች ሙሉ በሙሉ በሞጁላር ሥርዓተ ትምህርት ዘይቤ እየተሰጡ መሆኑ፣ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የት/ት መስኮች መከፈታቸው፣ የመደበኛ ተማሪዎች የሣይንስና ቴክኖሎጂ እና የማህበራዊ ሣይንስ ምጣኔ ከዕቅድ በላይ 72 ፡ 28 መድረሱ፣ በየካምፓሱ ለተማሪዎች ምቹ የጥናት ቦታዎች መዘጋጀታቸው፣ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች የመማሪያ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ስማርት መሆናቸው፣ ዓመታዊ የምርምር ሥራዎች ዳሰሳ አውደ ጥናት መካሄዱ፣ በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች የተሠሩ ምርምሮች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች መታተማቸው እና ነፃ የህግ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በኮንሶ፣ ጉማይዴና ጨንቻ ከተሞች ተጨማሪ ማዕከላት ተከፍተው ሥራ መጀመራቸው እንደ ስኬት የተመዘገቡ ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሴት መ/ራንን የምርምር አቅም ለማሳደግ ስልጠና መሰጠቱ፣ ከውጪ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ የምርምር ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው፣ በአካባቢው የሚገኙ ሁለት 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶችን ወደ ልህቀት ማዕከልነት ለማሸጋገር ፕሮፖዛል ተዘጋጅቶ እየተሠራ መሆኑ፣ አዲስ ለተቀጠሩ መ/ራን የማስተማር ሥነ -ዘዴ ስልጠና መሰጠቱ፣ ለ2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶች ሴት ተማሪዎች የህይወት ክህሎት ስልጠና መሰጠቱ፣ የመ/ራንና የሠራተኞች ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመታገል ያላቸው ግንዛቤ መጨመሩ፣ ለአመራሩ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች በመሰጠታቸው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የነበሩ ክፍተቶች መሻሻል ማሳየታቸው እና በተመረጡ የተማሪዎች አገልግሎት መስጫ ህንፃዎች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መግቢያና መውጫ ራምፖች መገንባታቸው እንዲሁም የውጪ አካላትን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እንዲሰሩ የሚያግዙ ተቋማዊ መረጃዎች በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በሩብ ዓመት መፅሔት፣ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ሚዲያ ተደራሽ መደረጋቸው ሌሎች በስኬት የተመዘገቡ አፈፃፀሞች ናቸው፡፡

በአንፃሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ሙሉ በሙሉ አለመወገዱ፣ የግንባታዎች መዘግየት፣ የምርምር ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ ለሴት  ተማሪዎች የሚሰጠው የማጠናከሪያ ት/ት በቂ አለመሆን፣ የማዕቀፍ ግዢዎች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ተገዝተው አለመቅረብ፣ የፋይናንስ ክፍያዎች መዘግየት፣ የሴት ተመራማሪዎችና አመራሮች ቁጥር በተፈለገው መጠን አለማደግ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

በግምገማ መድረኩ ሪፖርቱን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ውጤታማ አፈፃፀሞችን ይበልጥ ማጎልበትና ዝቅተኛ አፈፃፀም በታየባቸው የሥራ ዘርፎች ሁሉም አካላት ትኩረት ሰጥተው በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡