ዩኒቨርሲቲው 5ኛውን ‹‹ሣይንስ ለዘላቂ ልማት›› ሀገር አቀፍ ሲምፖዚዬም ከሚያዝያ 19-20/2010 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

ሲምፖዚዬሙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች እና መምህራን በሚያቀርቡት የጥናትና ምርምር ሥራዎች የሀሳብና የእውቀት ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ በተቋማት መካከል በተለያዩ መስኮች የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠናከር እንዲሁም ሣይንስና ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት የሚያበረክተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማጉላት የሚረዳ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ ተናግረዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በኢትዮጵያ የደን ልማት ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች፣ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ የአፈር ለምነት ባህሪያት፣ የአየር ንብረት ለውጥ በምርትና ምርታማነት እና በጤና ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በህፃናትና በአዋቂዎች ላይ የሚያስከትለው የጤና ችግር እና በአርብቶ አደር አካባቢ ያሉ ሴቶች ለደም ማነስ በሽታ ተጋላጭነት ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ እንደገለጹት ምርምሮቹ በሣይንስና ቴክኖሎጂ በመታገዝ የግብርና ምርትና ስርጭት ሂደቱን በማሳለጥ ከድህነት ለመላቀቅ እንዲሁም በጤናው ዘርፍ በሽታዎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

እንደ ዶ/ር ስምኦን ገለፃ ተለዋዋጭ ከሆነው የተፈጥሮ ዑደት ጋር ተራማጅ የሆነና ዘላቂ ልማት ማምጣት የሚችል ችግር ፈቺ ምርምር ማካሄድ ወሳኝ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት የሚካሄዱ ምርምሮች የትኩረት አቅጣጫዎችን መሠረት ያደረጉና በቀዳሚነት የማህበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ መሆን እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተርና ተመራማሪ ዶ/ር አጌና አንጁሎ የምርምር ሥራቸውን ሲያቀርቡ እንደተናገሩት የደን ልማት ለአየር ንብረት፣ ለውሃ አቅርቦትና ለእርሻ ምርታማነት ካለው አስተዋጽኦና ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው አንፃር የላቀ ፋይዳ ቢኖረውም እምብዛም ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ይህን ሂደት ለማሻሻል በሀገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማትም የበኩላቸውን ትብብርና ጥረት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶ/ር አብዱ መሐመድ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ በፈንገስ ምክንያት በለውዝ ምርት ውስጥ የሚፈጠረው ከፍተኛ የአፍላቶክሲን መጠን ለጉበትና ለተለያዩ የጤና ችግሮች አጋላጭ መሆኑን አብራርተው ከምርት ጀምሮ ተጠቃሚውጋር እስኪደርስ ሊደረግ የሚገባውን የመፍትሔ ሀሣብ አቅርበዋል፡፡

በሲምፖዚዬሙ በግብርና፣ በህክምናና ጤና ሣይንስ፣ በተፈጥሮ ሣይንስ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በብዝሃ ህይወት ጥበቃ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ 45 የምርምር ሥራዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ከተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ተቋማት፣ የምርምር ኢንስቲትዩቶችና ከዞኑ የመጡ እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎች እና መምህራን ተሳትፈውበታል፡፡