የዩኒቨርሲቲው ህግ ትምህርት ቤት ሚያዝያ 12/2010 ዓ/ም ከመምህራንና ተማሪዎች ጋር በመቻቻልና በህግ የበላይነት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡

የውይይቱ ዓላማ በኢትዮጵያ ያለውን የመቻቻል ሁኔታ ከፍ ከማድረግና የህግ የበላይነትን ከማስጠበቅ አንፃር የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተማሪዎች የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ብሎም ለተግባራዊነቱ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማስቻል እንደሆነ የት/ቤቱ  ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

መቻቻል ጠንካራ ማህበረሰብ ለመፍጠር መነሻ ነው ያሉት የዕለቱ እንግዳ የፍልስፍና ምሁር  ዶ/ር  ዳኛቸው አሰፋ በመቻቻል ፅንሰ ሀሳብ፣ ታሪካዊ ዳራ፣ አረዳድና አተገባበር እንዲሁም በህግ የበላይነት ላይ ገለፃ  አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው በሀይማኖቶች፣ በብሔረሰቦችና በፖለቲካው ማኅበረሰብ መካከል ያሉ የተለያዩ አስተሳሰቦችን በመቀበል ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶች በመኖራቸው ምሁራኑ ያንን ክፍተት አጣጥመው መረዳትና መቻቻል አለባቸው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መካከል የመቻቻል ባህልን ለማዳበር ተማሪዎች መልካም ሥነ- ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ፣ የአንዱን ብሔር ሌላኛው እንዲያከብር፣ ባህላዊ ውርርስ እንዲፈጠር እና በተለያየ መንገድ የብሔር መግባባትና ትውውቅ እንዲኖር እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በቀጣይም ተከታታይ የውይይት መድረኮችንና ፎረሞችን አዘጋጅቶ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ምሁራንን በመጋበዝ የመቻቻል ልምድን ለማዳበር ትምህርት ቤቱ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተጠቁሟል፡፡ በውይይቱ በርካታ አስተየየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡