የማህበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በጋሞ ጎፋ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለሚያስተምሩ 35 የጋሞኛ ቋንቋ መምህራን ከመጋቢት 14 – 16/2010 ዓ/ም ድረስ ለ3  ተከታታይ ቀናት የክህሎት ማሻሻያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ኃላፊ መ/ር መሀመድ ሹሬ እንደገለፁት በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመድበው ጋሞኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራን የጋሞኛ ቋንቋ የሚናገሩ ወይም ለቋንቋው ቅርብ የሆኑና ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተወጣጡ እንጂ በዘርፉ የተመረቁ አይደሉም፡፡ በመሆኑም በሚያስተምሩበት ጊዜ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ስልጠናው አስፈላጊ ነው፡፡

የንግግርና የማዳመጥ ክህሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና የሰጡት የጋሞኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ዶ/ር ሳሙኤል ጎንደሬ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በቋንቋው የሚሰጠውን ትምህርት አዳምጠው የተረዱትን በተለያየ መንገድ እንዲፅፉ ወይም እንዲናገሩ በማድረግ ንግግር አዳምጦ የመረዳት ክህሎታቸውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ሳሙኤል አክለውም በቋንቋው የተፃፉ መፅሃፍትም ሆኑ በዘርፉ የተማሩ ምሁራን ባለመኖራቸው መምህራንን ለማብቃት በተደጋጋሚ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር ሰልጣኞቹ ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በሥራ ላይ ማዋላቸውን ግምገማ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የንባብና የፅሁፍ ክህሎትን አስመልክቶ ስልጠና የሰጡት የጋሞኛ መምህር አሰልጣኝ ኤርምያስ በፈቃዱ ጋሞኛ ቋንቋ የእንግሊዝኛ ፊደላትን የሚጠቀም በመሆኑ በፅህፈትም ሆነ በንባብ ወቅት እንዳይጋጭባቸው መምህራኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውና ተማሪዎችም በልምምድ ማዳበር እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ መምህር ኤርምያስ ገለፃ ቋንቋው ገና ታዳጊ በመሆኑ ሌሎች ቋንቋዎች የደረሱበት ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም በቋንቋው የተለያዩ ፅሁፎችን ለማዘጋጀት መ/ራን በዕውቀትና በክሂሎት የበቁ መሆን የሚኖርባቸው ሲሆን በቋንቋው ረገድ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በመለየት ትኩረት ተደርጎ ሊሠራበትም ይገባል፡፡

የማህበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ በተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች በርካታ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን የገለፁት የኮሌጁ ዲን አቶ ሙሉጌታ ደበሌ የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ በቀጣይ ተመሳሳይ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው የቋንቋ ክህሎትን ለተማሪዎቻቸው እንዴት ማስተማር እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤን የፈጠረላቸው መሆኑን ገልፀው በማስተማር ረገድ የሚፈጠሩ ስህተቶችን ለማረም ያግዘናል ብለዋል፡፡