በሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ት/ቤት የከፍተኛ ዲፕሎማ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በዩኒቨርሲቲው ሥር ካሉ ሳተላይት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ከተወጣጡ የከፍተኛ ዲፕሎማ አስተባባሪዎችና አሰልጣኞች እንዲሁም የት/ቤት ዲኖች ጋር ሚያዝያ 27/2010 ዓ/ም በሀዋሳ ከተማ ዓመታዊ ወርክ ሾፕ አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በመድረኩ የሁሉም ሳተላይት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ የተመዘገቡ መልካም አፈፃፀሞች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሀሣቦች በHDP አስተባባሪዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በዋናነት ሠልጣኞችና የተቋማት ኃላፊዎች ለሥልጠናው የሚሰጡት ትኩረት አናሳ መሆኑ፣ የተደራጁ የሥልጠና ማዕከላት በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው፣ በቂና ወጥ የማበረታቻና የሥልጠና ሥርዓት አለመዘርጋቱ እንዲሁም በማሠልጠኛ ሞጁሎች ላይ የሚታየው የይዘት ድግግሞሽ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች መሆናቸውን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል ፡፡

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ት/ቤት ዲን ዶ/ር ኢዮብ አየነው መንግሥት የትምህርት ጥራትንና ተገቢነትን ለማረጋገጥ ለመምህራን ሙያዊ ዕድገት ትኩረት መስጠቱን ገልፀው ለዚህም ይረዳ ዘንድ በኮሌጆችና በዩኒቨርሲቲዎች የከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም (HDP) ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ተከፍተው የመምህራንን ሙያዊ ብቃት ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ወርክ ሾፑ በዩኒቨርሲቲው እንዲሁም በአራቱ ሳተላይት ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም እስካሁን ባለው የሥራ ሂደት የተከናወኑ መልካም ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሣቦች ላይ በመወያየትና ልምድ በመለዋወጥ በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ አቅጣጫ ከማመላከት አኳያ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ት/ቤት የከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አንለይ ብርሃኑ እንደተናገሩት እ.ኤ.አ ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ኮሌጆችንና ዩኒቨርሲቲዎችን በመያዝ የከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም (HDP) የማስተባበር ኃላፊነቱን እየተወጣ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት 881 መምህራንን በፕሮግራሙ አስመርቋል፡፡

አሁን ላይ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ለአሠልጣኞችና ሠልጣኞች የማበረታቻና ዘዴ ቀይሶ ፕሮፖዛል ያዘጋጀ ሲሆን ከት/ት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የHDP ማሠልጠኛ ሞጁሎች ላይ ክለሳ በማድረግ ሥልጠናው ውጤታማ እንዲሆን እየሠራ ይገኛል፡፡

በወርክ ሾፑ ከአርባ ምንጭ፣ ወ/ታ ሶዶ እና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከአርባ ምንጭና ሆሳዕና መምህራን ት/ት ኮሌጆች የተወጣጡ የHDP አስተባባሪዎች፣ አሰልጣኞችና የት/ቤት ዲኖች ተሳትፈዋል፡፡