በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እና የማኅበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጆች አዘጋጅነት 5ኛው ምርምር ለልማት ሀገር ዓቀፍ ዓውደ ጥናት ከግንቦት 03-04/2010 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ፣ ሀገረሰባዊ እምነትና ሀገር በቀል እውቀት፣ ባህልና ቅርስ፣ ሰብዓዊ መብትና የፍትህ ሥርዓት እንዲሁም አነስተኛ ኢንተርፕራይዝና የግብር ሥርዓት ለዓውደ ጥናቱ የተመረጡ 20 ምርምሮች ካተኮሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ ‹‹በዩኒቨርሲቲው የቀረቡት ምርምሮች ከተሳታፊዎች የሚገኙ አስተያየትና የማሻሻያ ሀሣቦችን በማካተት በማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በኩል ወደ ፕሮጀክት እንዲቀየሩ እንሠራለን፤ በዚህም ጥናታዊ ጽሑፎች በመድረክና በሸልፍ ተወስነው እንዳይቀሩ ጥረት ይደረጋል›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ተሾመ ‘‘Friut Based Farming System and Threatened Landscape: A case Study from the Wetlands of Abaya-Chamo Basin,Southern Ethiopia’’ በሚል ርዕስ የፍራፍሬ እርሻዎች በአባያና ጫሞ ሐይቆች ውኃ ጠገብ አካባቢና በሐይቁ ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በጽሑፉ እንደተመለከተው የአባያና ጫሞ ውኃ ጠገብ አካባቢ እርጥበታማና ለእርሻ ሥራ ምቹ በመሆኑ እስከ ሐይቁ ጫፍ ድረስ እየታረሰ ነው፡፡ ይህም ሐይቁን በደለል በመሙላት ውኃው ወደ ውጪ እንዲሸሽ እያደረገው ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የአመለካከት ችግር እንዲሁም ድርጊቱን ለማስቆም የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ችግሩን እያባባሰው በመሆኑ መፍትሔ ለማበጀትና ሐይቆቹን ከጥፋት ለመታደግ ሁሉም የሚመለከተው አካል ከፍተኛ ትኩረት መስጠትና በአፋጣኝ ወደ ተግባር መግባት ይኖርበታል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ የምርምር ተቀዳሚ ተግባር ለችግሮች መፍትሔ ማፈላለግ እና ዘርፈ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር፣ በማላመድና በማሸጋገር የማኅበረሰቡን አኗኗር ማሻሻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህን መሰል ዓውደ ጥናት ማሰናዳቱ የምርምርን ግብ ከማሳካት አኳያ በየዩኒቨርሲቲና የምርምር ተቋማት የሚሠሩ ምርምሮች ለሚመለከተው አካል እንዲደርሱ፣ ተጨማሪ ምርምር ለሚያደርጉ ባለሙያዎች ግብዓት እንዲሆኑና ተግባራዊነታቸውን ለማጠየቅ እንደሚረዳም ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ስምኦን አክለውም ከዚህ ቀደም እንደነበረው ልምድ ምርምሮች የመድረክ ፍጆታ እና የመርሃ ግብር ማሟያ ሳይሆኑ ወደ ማኅበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አድገው የማህበረሰብ ተጠቃሚነቱ ከፍ እንዲል መሥራት አለብን፤ ይህንን ከማሳካት አኳያም ከጊዜ ወደ ጊዜ አዎንታዊ ለውጦችን እያየን ነው ብለዋል፡፡ ካለፈው ጊዜ ልምድ በመቅሰም በዘንድሮው ዓውደ ጥናት የቀረቡ ምርምሮች አንፃራዊ በሆነ ደረጃ በፕሮጀክት ተቀርፀው ወደ ኅብረተሰቡ ሊወርዱና ለፖሊሲ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምህርት ድርብ ወርቅ ብፁ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ‹‹ሀገረሰባዊ እምነት እና ሀገር በቀል እውቀት ለሥነ-ምህዳር እና አካባቢ ጥበቃ ያላቸው አስተዋፅኦ›› የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በአማራ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ በሆነው አዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ላይ ተሠርቷል፡፡ የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው የአዊ ማኅበረሰብ ትልልቅ ዛፎች፣ ጫካዎች፣ የውኃ ምንጮች፣ ፏፏቴዎችና ተራሮች ላይ የሚያከናውናቸው ሀገረሰባዊ የእምነት ሥርዓቶች የአካባቢ ሥነ-ምህዳር እንዲጠበቅ የሚያደርጉ ሲሆን በአንፃሩ ፀረ-አረም ኬሚካሎች፣ ዘመናዊ ማዳበሪያ፣ የባህር ዛፍ ተክል እና ሌሎች ዘመን አመጣሽ የህዝባዊ ባህል ጫናዎች ሥነ-ምህዳሩ እንዲበከል ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው፡፡ በአካባቢ ጥበቃ እና ሥነ-ምህዳር ልማት ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የማኅበረሰቡን ሀገር በቀል እውቀትና ሀገረሰባዊ ልማድ መሠረት ቢያደርጉ የተሻለ ውጤት ላይ መድረስ እንደሚቻል አጥኚዋ የማጠቃለያና የይሁንታ ሀሣቦች ሰጥተዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ አቶ አብርሃም በላይ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ‘‘Climate Change Impacts and Adaptation Strategies by Smallholder Farmers in the Central Rift Valley Ethiopia’’ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እና አርሶ አደሮቹ ተጽዕኖውን የሚቋቋሙበትን መንገድ ዳስሷል፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም በተለመደው የአስተራረስ ዘዴ ተጠቅሞ ውጤታማ ለመሆን ይቸገራል፡፡ ስለሆነም ወቅቱን የዋጀ የአስተራረስ ዘዴና የግብርና ግብዓት ተጠቃሚ መሆን ያስፈልገዋል፡፡ የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ አርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጡን ተፅዕኖ ለመቋቋም አፈራርቆ መዝራት፣ የዘር ወቅትን ማስተካከል፣ የውኃና አፈር ጥበቃ፣ ዛፍ መትከልና የመሳሰሉ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ የአርሶ አደሮቹን ባህላዊ የመፍትሔ እርምጃ ውጤታማ ለማድረግ የቴክኖሎጂ እና የፖሊሲ እገዛ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

አቶ አብርሃም ምርምርን አስመልክቶ ሲናገሩ ችግሮች ተነቅሰው የመፍትሔ ሀሣብ እንዲሰጥበት፤ ሀሣቦቹም በተለያዩ አካላት ተለይተው ወደ ተግባር እንዲገባ የሚሠሩ ናቸው ይላሉ፡፡ እንደ ግል ምልከታቸውም አብዛኛው የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች በዓመቱ መጨረሻ ላይ መሰል ሲምፖዚየሞችን ያዘጋጃሉ፤ ተመራማሪዎች ሥራቸውን ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን ምርምሮቹ መሬት ወርደው ያመጡትን ለውጥ ለመለካት አልተሠራም፡፡ ምርምሮቹ በርካታ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት የወጣባቸው እንደመሆኑ ያመጡትን ተጨባጭ ለውጥ መለካት አስፈላጊ ነው፡፡

በዓውደ ጥናቱ የአዘጋጁ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የመዳ ወላቡ፣ ሀዋሳ፣ አዲግራት፣ ጅግጅጋ፣ አክሱም፣ ወሎ፣ መቐለ እና ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የወልዲያ መ/ት ኮሌጅ፣ ትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ አላማጣ ግብርና ምርምር ማዕከል እና የጋሞ ጎፋ ዞን ትምህርት መምሪያ ተመራማሪዎችና የትምህርት ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡