የዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶች ምርምር ዩኒት ከሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ጋር ባህል፣ ታሪክ፣ ተፈጥሮና ቱሪዝምን በምርምር፣ በዶክሜንቴሽንና በፊልም ጥበብ ለማበልፀግና ለማስተዋወቅ የሚረዳ የመግባቢያ ስምምነት ግንቦት 04/2010 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን መጠበቅ፣ ማልማትና ማስተዋወቅ፣ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት፣ ምርምሮች ማካሄድ፣ ቅርሶችና የቱሪዝም ሀብቶችን መሰነድ፣ ዶክሜንተሪና ፊቸር ፊልሞችን መሥራት፣ ዓውደ ጥናትና ሲምፖዚየሞችን ማዘጋጀት እንዲሁም የእውቀትና የሰው ኃይል ልውውጥ ማድረግ በስምምነቱ የ5 ዓመት ቆይታ የሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራት ናቸው፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ ስምምነቱን አስመልክተው ሲናገሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከኢንደስትሪው ጋር ትሥሥር በመፍጠር በምርምር የሚገኘውን እውቀት በተግባር መግለጥ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ የመዝናኛ ኢንደስትሪ አካል ከሆነው ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ጋር የተገባው ውልም የዚህ እሳቤ ውጤት ነው፡፡

‹‹ራስን መፈለግ፣ መሆን፣ መግዛት›› የሚል መፈክር ያለው ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ተፈጥሮ፣ ባህልና ታሪክን በሥነ-ጥበብ ከሽኖ ለማንነት ግንባታ ለማዋል አልሞ መቋቋሙን የፕሮዳክሽኑ መስራችና ባለቤት የፊልም ጥበብ ባለሙያው ሚካኤል ሚሊዮን ተናግሯል፡፡ ሰውኛ ራዕዩን ለማሳካትም ከከፍተኛ የትምህርት እና የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል፡፡

ሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር 121ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ከየካቲት 20-23/ 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲያከብር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአድዋ ጦርነትና ድሉን የሚዘክር ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብና የደራሼ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን የ‹ፊላ› ጨዋታን በጣይቱ ሆቴል እንዲያቀርብ በማጓጓዝና በማስተባበር መሳተፉ ይታወሳል፡፡