የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ት/ት ክፍል እና ከጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ጋር በመተባበር ከዞኑ 17 ወረዳዎችና 3 ከተማ አስተዳደሮች ለተወጣጡ የቱሪዝም ባለሙያዎች ከግንቦት 6-8/2010 ዓ/ም የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማልማትና ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ (Destination Development)፣ መዳረሻ ቦታዎችን ማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ (Tourism Marketing & Promotion )፣ እንዲሁም የእንግዳ አቀባበል (Hospitality) በሥልጠናው የሦስት ቀናት ቆይታ የተዳሰሱ ይዘቶች ናቸው ፡፡

በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ርት ትዕግስት ኃይሌ እንደተናገሩት የሥልጠናው ዋና ዓላማ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች በብዛት በዘርፉ የሠለጠኑ ባለመሆናቸው በባለሙያዎቹ ላይ የሚስተዋለውን የዕውቀትና የክህሎት ክፍተት መሙላት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሥልጠናው የባለሙያዎቹን አቅም በማጎልበት የዞኑን የቱሪስት መስህቦች ለማልማትና ለማስተዋወቅ እንዲሁም የጎብኚዎችን አቀባበል በማሻሻል ዞኑ ከዘርፉ ማግኘት ያለበትን ጥቅም እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ ሚናው የጎላ ነው ፡፡

በሥልጠናው ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች በቆይታቸው ከዚህ ቀደም ከማያውቋቸው በርካታ አዳዲስ ፅንሰ ሃሳቦች ጋር እንደተዋወቁ ገልፀው ይህም ለሥራቸው ስኬት አጋዥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ መስህቦችን ከማልማት፣ ከማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ከማድረግ አኳያ ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ዞኑ ከዘርፉ በአግባቡ እንዲጠቀም የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ቃል ገብተዋል፡፡

ሥልጠናው በቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህራን የተሰጠ ሲሆን ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡