3ኛው የባህልና ቱሪዝም ፌስቲቫልና ኤግዚቢሽን ‹‹የባህልና ቱሪዝም ሀብቶቻችን ለዘላቂ ልማትና ለአንድነታችን›› በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል፣ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ በጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደርና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ከሚያዝያ 25-30/2010 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና  አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ እንደተናገሩት የጋሞ ጎፋ ዞን በአራቱም አቅጣጫ የሚታዩ ማራኪ የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ ቅርሶችና በርካታ ባህላዊ እሴቶች የሚገኙበት በመሆኑ እነዚህ ባህላዊ እሴቶችና ቅርሶች ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት ልንሠራ ይገባል፡፡ አስተዳዳሪው አክለው አያት ቅድመአያቶቻችን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩዋቸውና በአብሮነት ውስጥ የዘለቁ የባህል እሴቶች የመበረዝና በሌሎች ተፅዕኖ ሥር የመውደቃቸው አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ በመጤ ባህል እንዳይበረዙ መከላከል ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እልፍነሽ ኃይሌ እንደገለጹት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቱባ ባህላዊ እሴቶችና መገለጫዎች በማበልፀግ አንዱ የሌላውን ወግ እንዲያውቅና እንዲያከብር እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ማስቻል ይጠበቅብናል፡፡ በሌላም በኩል አዲሱ ትውልድ ሀገር ተረካቢ እንደመሆኑ መጠን ሀገራዊ አንድነትን በጋራ የማጎልበት ጉዞ ባህሉንና ማንነቱን ጠንቅቆ እንዲያውቅና እንዲያከብር የዚህ ዓይነቱ ዝግጅት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አክመል መሐመድ በበኩላቸው የባህል እሴቶችንና የቱሪዝም ሀብቶችን ሳይበረዙ በተደራጀ መንገድ ለማስተዋወቅና ለማበልፀግ እንዲሁም በክልሉ ሕዝቦች መካከል አንድነትን፣ መቻቻልንና መከባበርን ለማጠናከርና ለማጎልበት ቢሮው በትጋት ይሠራል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት የባህልና ቱሪዝም ዘርፉን ከማልማትና ከማሳደግ አኳያ ዩኒቨርሲቲው በዕውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል በማፍራትና በዘርፉ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ባህል የአንድን ማህበረሰብ የህይወት ልምድ የሚያጠቃልል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚያከናውናቸውን የምርምር ውጤቶች ወደ ማህበረሰቡ በማሸጋገር የማህበረሰቡን ህይወት ሊያሻሽሉ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዝግጅቱ የባህል ትርኢቶች፣ የብሔር ብሔረሰቦች አዝናኝ ባህላዊ ጭፈራዎችና ሙዚቃዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን በተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻ የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡