የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲው ግብርና ሣይንስ ኮሌጅ በአርባ ምንጭ ከተማ የፀረ-እብድ ውሻ በሽታ ክትባት ዘመቻ ከግንቦት 10-11/2010 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

የእብድ ውሻ በሽታ (Rabies) በውሾችና ድመቶች አማካኝነት ወደ ሰው የሚተላለፍ አደገኛ በሽታ በመሆኑ በከተማዋ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በፍጥነት ለመቆጣጠር እንዲቻል የክትባት ዘመቻው መከናወኑን በኮሌጁ የእንስሳት ጤና ሣይንስ መምህርና የክትባቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር እድገት አባይነህ ተናግረዋል፡፡ ክትባቱ በአርባ ምንጭ ከተማ በሚገኙ 11 ቀበሌያት መሰጠቱንና በቀጣይም ሌሎች ወረዳዎችን እንደሚያዳርስ ዶ/ር እድገት ጠቁመዋል፡፡

 

የከተማው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታከለ ከበደ የክትባቱ መሰጠት የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ምን ያህል ተግቶ እየሠራ እንደሚገኝ የሚያሳይ መሆኑን ተናረዋል፡፡ በሽታውን ከወዲሁ ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው የሚቻለውን እንዲያደርግ በተደጋጋሚ በጠየቅነው መሰረት ተሳክቶ ለውጤት መብቃቱ እጅግ የሚያስደስት ሲሆን በቀጣይም ከጎናችን እንደማይለይ እምነታችን ነው ብለዋል፡፡

የቤሬ ቀበሌ ነዋሪዋ ወ/ሮ እቴነሽ ሁቃ ከዚህ ቀደም እንስሳት ሲታመሙባቸው ግብርና ጽ/ቤትና የእንስሳት ጤና ተቋማት በመውሰድ ማሳከማቸውን ገልጸው በተለይ ውሻ በተደጋጋሚ ጆሮዎቹንና ጅራቱን ሲያጥፍ እንዲሁም በአፉ አረፋ ከታየ የህመም ምልክት መሆኑን እንደሚረዱ ገልጸዋል፡፡ የውሾች ይህን ክትባት ማግኘትም ጤነኛ እንዲሆኑና በእነሱ ምክንያት በሰዎች ላይ ሊመጣ የሚችለውን የጤና ስጋት ይቀንሳል ብለዋል፡፡

በክትባት ዘመቻው የጋሞ ጎፋ ዞን እንስሳትና ዓሣ ሀብት ባለሙያዎች፣ የከተማዋ ግብርና ጽ/ቤት ባለሙያዎች እና የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሣይንስ ኮሌጅ የእንስሳት ሣይንስ ትምህርት ክፍል መምህራንና የ2ኛና 3ኛ ዓመት ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከ1500 በላይ ውሾችና ድመቶች ተከትበዋል፡፡ በቀጣይም ባለቤት አልባ ውሾች እንደሚወገዱ ተገልጿል፡፡