የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ አካባቢ ማህበረሰብና አስተዳደር ትስስር ፎረም ግንቦት 15/2010 ዓ.ም ዉይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ ከጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ከ4ቱ ክፍለ ከተማዎችና 11 ቀበሌያት የመጡ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በአርባ ምንጭ ከተማ በተለያዩ ማዕዘናትና በመሃል የተመሰረቱት 5 ካምፓሶች ለከተማዋ እድገትና ውበት የጎላ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በሣውላ ከተማም እንዲሁ ከሁለት አቅጣጫ ወደ ከተማዋ መግብያ ላይ ካምፓስ መቋቋሙ ለከተማዋ እድገት አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተከታታይና ርቀት ትምህርትም መርሃ ግብሮች በመከፈታቸው በመደበኛው ፕሮግራም የመማር እድል ያላገኙ ወጣቶችና የመንግሥት ሠራተኞች የመማር እድል አግኝተዋል፡፡

የካምፓሶቹ መስፋፋት መልካም ጎኖች እንደተጠበቁ ሆነው ፈታኝ ሁኔታዎችን በአንክሮ መገንዘብና ለማሻሻል በትኩረት መሥራት ለአካባቢውም ሆነ ለሀገሪቱ እድገት ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ ስለሆነም መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች በጋራ በመገምገም ለወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ፎረሙ ውይይት ማካሄዱ አስፈላጊ ነው፡፡

የተቋማዊ ለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በሀይሉ በፈቃዱ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተጠቀሰው የአካባቢውና የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ተባብረው በመሥራታቸው የ2010 ዓ/ም ትምህርት አንድም ቀን ሳይቆራረጥ በሰላም ተከናውኗል፤ አልፎ አልፎ ችግሮች ሲከሰቱ ሳይስፋፉ በውይይት መፍታት ተችሏል፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ለአደንዛዥ ዕፅ ተጋላጭነትን ለመቀነስና ለመከላከል ከከተማውና ከዞኑ የተለያዩ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት የክትትል እና ሺሻ ቤቶችን የማዘጋት ሥራ ተሠርቷል፡፡

በተጨማሪም Big Sisters እና Big brothers ክበባትን በማደራጀት እንዲሁም በየኮሌጁ ያሉ ክበባት የHIV/AIDS ጉዳይን አካተው እንዲሠሩ የማቀናጀት ሥራ  ተሠርቷል፤  ሴቶችን ከጾታዊ ትንኮሳ ለመከላከል  Anti Sexual Code of Conduct በማዘጋጀት በዓመቱ መጀመሪያ ለተማሪዎች በሁሉም ዶርሞች እንዲደርሳቸው ተደርጓል፤ HIV/AIDSን ከመከላከል አኳያ ለሴት ተማሪዎች ዜሮ ፕላን በሚል መርህ በአምስቱ ግቢዎች የህይወት ክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ችግሮች ሲከሰቱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ ምላሽና መፍትሄ አለመስጠት እንዲሁም  በዩኒቨርስቲዉ ዙሪያ ያሉ የሺሻ፣ የጫት መሸጫና መቃሚያ ሥፍራዎች እና ግሮሰሪዎች ተማሪዎች ለኤች አይቪ/ ኤድስና ላልተፈለገ እርግዝና እንዲጋለጡ ምክንያት መሆን ዩኒቨርሲቲው ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመከላከልና ሌሎች ዘርፎች በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ ምግባረ ብልሹና ከዩኒቨርሲቲው የተሰናበቱ ተማሪዎች ለሱስና ለስርቆት እንዲመቻቸው ከተማ ቤት ሲከራዩ ህብረተሰቡ ለዩኒቨርሲቲው ጥቆማ ለመስጠት በበቂ ሁኔታ አለመተባበር፣ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ትንኮሳዎችን ለመከላከል በሚደረጉ ተግባራት ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ አናሳ መሆን፣ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ቢደረግም ሺሻን በሚመለከት የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የፀጥታ ዘርፉ የሺሻ ዕቃውን ከመውረስ ውጪ ችግሩን በሚፈታ መልኩ ዘለቄታዊ እርምጃ አለመውሰድ ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው፡፡

ችግሮችን ለማስወገድ የዩኒቨርሲቲና የአካባቢ ማህበረሰብ ትስስርን የበለጠ በማጠናከር በቅንጅት መሥራት፣ የከተማው ወጣቶችና ተማሪዎች የአደንዛዥ ዕፅ ሰለባ እየሆኑ መምጣታቸው የዩኒቨርሲቲውን ቫይረሱን የመከላከል ሥራ ስለሚገታው የከተማውና የዞኑ መንግሥት ህግና ደንብ በማውጣት ወጣቶቹን የሚታደጉበትን ሁኔታ መፍጠር፣ በሚያጋጥማቸው ችግሮች ላይ በመመስረት በየጊዜው የተሻሉ አሰራሮችን መዘርጋት የሚያስፈልግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው ስርቆት የሚፈጽሙና ተባባሪ አካላትን ማጋለጥና ለህግ ማቅረብ፣ ተማሪዎችን ላልተፈለገ ምግባር የሚጋብዙ ሁኔታዎችን ማስወገድ፣ ድብደባና ትንኮሳን መከላከል ብሎም ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ከህግ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ጫሞ ካምፓስ አካባቢ ዲች ሞልቶ ለሚያልፈው ፍሳሽ መፍትሔ መፈለግ፣ የተማሪዎችን ተረፈ ምግብ  ለመጠቀም ሲባል ግቢ በሚገቡ ግለሰቦች የሚፈፀም ስርቆትና ሕገ-ወጥ ተግባርን መከላከልና ለድርጊቱ ተባባሪ የሆኑ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ፣ ሰዓት እላፊ ሁከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩ አንዳንድ ምግባረ ብልሹ ተማሪዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ፣ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል በአትኩሮት መስራት እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማት የሚያደርጓቸው ፕሮግራሞች የተማሪዎችን ግቢ የመግቢያ ሰዓት ያገናዘበ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ማድረግ የሚገባው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡