የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከጋሞ ጎፋና ከሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞኖች ለተወጣጡ የወረዳ ከፍተኛ የእንስሳት እርባታ ባለሙያዎች ከግንቦት 14-18/2010 ዓ/ም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የእንስሳት እርባታን ለማዘመን የሚረዳ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው አልጀብሪክ ማቲማቲክስ (Algebric Mathematics) እና የኮምፒውተር ሶፍት ዌር አጠቃቀም ተካተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የእንስሳት እርባታ ባለሙያዎቹ ከስልጠናው ያገኙትን ምግብን በማመጣጠን፣ በማመዛዘንና በማደራጀት የእንስሳት እርባታን በዘመናዊ መልኩ አጎልብቶ በአጨር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ መሆን የሚያስችል ግንዛቤ ለሌሎች በአካባቢያቸው ላሉ የልማት ሠራተኞችና የግብርና ባለሙያዎች በማካፈል በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነትና የገበያ መናር ለማረጋጋት ስልጠናው መዘጋጀቱን የኮሌጁ ዲን አሰልጣኝ ዶ/ር ይስሀቅ ከቸሮ ተናግረዋል፡፡

የሰልጣኞቹ የትምህርት ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ መሆኑ የስልጠናውን መልዕክት በጥልቀት ተረድተው   ለሌሎች በአካባቢያቸው ለሚገኙ የእንስሳት እርባታና የልማት ሰራተኞች በማካፈልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር በመቀየር  ውጤታማ መሆን  እንደሚያስችላቸው ዶ/ር ይስሀቅ አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም በተወሰኑ የደቡብ ኦሞ እና የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎችን ጨምሮ ሌሎች ያልተሳተፉ የጋሞ ጎፋ ዞን ወረዳዎች በተመሳሳይ አጀንዳ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡