ዩኒቨርሲቲው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 7ኛ ዓመት ክብረ በዓል ግንቦት 15/2010 ዓ.ም በድምቀት አክብሯል፡፡ በዕለቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ሁኔታ ገለፃን መነሻ በማድረግ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የቲ-ሸርት ሽያጭ፣ የቦንድ ግዢና በቀን 19/09/2010 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሦስት ዙሮች ሙሉ ደመወዙንና በልዩ ሁኔታ የቦንድ ግዥ በመፈጸም፣ በግድቡ ስም የታተመ የሎተሪ ቲኬት በመግዛት፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ሦስት ዙር ከቀለባቸው ቀንሰው የሎተሪ ቲኬት በመግዛት በድምሩ 32.64 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ውሃ ዘርፍ ምሁራን በግድቡ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተዘጋጅተው ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተወከሉ አካላት የግድቡ ግንባታ የሚካሄድበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ጉብኝት ማካሄዳቸውን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል እንደተናገሩት ግድቡ በሀገራችን የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠል፣ የአካባቢውን የከርሰ ምድር ውኃ መጠን ለመጨመር፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ የዓሣ ሀብት ምርት መጠንን ለማሳደግ እንዲሁም አሁን ያለውን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት  ም/ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር በሻ ሞገስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ እስከ አሁን ድረስ ያለውን የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ/ የደረሰበት ደረጃ ፣ የግድቡ መጠን፣ ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል መጠን እንዲሁም የታችኛውና የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በግድቡ እና በአባይ ወንዝ ዙሪያ ባላቸው አመለካከትና ግንዛቤ ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ግድቡ በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብና በራሳችን ባለሙያዎች የሚገነባ በመሆኑ በህዝቡ መካከል የአብሮነትንና የይቻላል መንፈስን የፈጠረ ታላቅ ክንውን ከመሆኑም በላይ ሲጠናቀቅ የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ዶ/ር በሻ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የቦንድ ግዢ በይፋ የተጀመረ ሲሆን የ 145 ሺህ ብር የቦንድ ግዢ ተፈጽሟል፡፡