በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት “በተፈጠረው ዕድል ማህበረሰቡን እናገልግል“ በሚል መሪ ቃል 3ኛው ዓመታዊ የማህበረሰብ ሳምንት በአውደ-ርዕይና በማህበረሰብ ውይይት ከሰኔ 19-22/2010 ዓ.ም በድምቀት ተከብሯል፡፡ የበዓሉ ዓላማ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የተሰሩ ስራዎችን ለማህበረሰቡ ማሳወቅና የነበሩትን ክፍተቶች ተገንዝቦ በቀጣይ ምን ማድረግ እንደሚገባ ከማህበረሰቡ ጋር  በመወያየት አቅጣጫ ማስያዝ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በመክፈቻ ንግግራቸው የሀገራችንን እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይል ልማት ወሳኝ ሚና እንዳለው በመገንዘብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለልዩ ልዩ ስራ መስኮች ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማፍራት፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድና ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ ለሀገሪቱ እድገት እንዲሰሩና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ አደራ ተጥሎባቸዋል ብለዋል፡፡

ይህን በመገንዘብ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች በስፋት ሲሰሩ ቆይተው አሁን ለስኬት መብቃታቸው የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የማህበረሰብ አገልግሎቶችንና የምርምር  ማዕከላትን  በማጠናከርና በመመስረት እንዲሁም ተማሪዎች ለፈጠራ  ስራ ተነሳስተው ስኬታማ መሆን እንዲችሉ ጥረት ያደርጋልም ብለዋል፡፡

በበዓሉ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በ2010 የበጀት ዓመት ያከናወናቸው ተግባራት በዝርዝር ቀርበው የታዩ ክፍተቶችን በቀጣይ ለማስተካከል በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ከማህበረሰቡ ጋር በስፋት ውይይት ተደርጓል፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ ከሰራቸው ተግባራት መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው አጎራባች የገጠር ቀበሌያት የፀሀይ ኃይል (Solar Project) ለነዋሪዎች ማዳረስ፣ የትምህርት ጥራት በሚገባ ባልተዳረሰባቸው የደቡብ ኦሞና የጋሞ ጎፋ ዞኖች የSTEM(Science Technology engineering and Mathematics) ትምህርቶችን ጥሩ አፈጻጸም ላላቸው ተማሪዎች በክረምት መርሃ-ግብር በኮምፕዩተር የታገዘ ትምህርት መስጠት፣ ለአቅመ-ደካሞች ነጻ የህግ ምክርና ጥብቅና የመቆም አገልግሎት መስጠት፣ የአካባቢ ጥበቃና የተጎዱ ስነ-ምህዳሮችን መልሶ ማልማት፣ የመደበኛ የትምህርት ዕድል ላላገኙ ዜጎች የተቀናጀ ተግባር ተኮር ትምህርት መስጠት፣  ትምህርት ቤቶችን በስልጠናና በገንዘብ መደገፍና ተማሪዎችን በምርምርና በፈጠራ ስራ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ በማህበረሰብ አገልግሎት ማዕቀፍ ውስጥ ዋና ተግባር ማህበረሰቡን ማገልገል በመሆኑ የገባነውን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር የማህበረሰቡን ችግርና አኗኗር ተመልክቶ መፍትሄ ለመስጠት ዩኒቨርሲቲው እቅድ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህም በቆላማ አካባቢዎች የሚከሰቱ የተዘነጉ በሽታዎች ዳግም እንዳይከሰቱና ለመቆጣጠር እንዲቻል ዩኒቨርሲቲው በጋሞ ጎፋ ዞንና በደቡብ ኦሞ ዞን ቆላማ ቦታዎች ጥናቶችንና ምርምሮችን አካሂዷል፡፡ በተለይ በደቡብ ኦሞ ዞን በተመረጡ 3 ወረዳዎች በተደረገው ጥናት መሰረት 75 የሚሆኑ የከተማው ነዋሪዎችና 25 የሚሆኑ የአርብቶ አደር ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸው ታውቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም እነዚህን በሽታዎች ለመቆጣጠር ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ዶ/ር ስምኦን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ከ2010 ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙና የምርምርና የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ተማሪዎች የሰሯቸው የፈጠራ ስራዎች ከበዓሉ መክፈቻ ቀን ጀምሮ ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

አውደ-ርዕዩን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባላት፣ የጋሞ ጎፋ ዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ከአርባ ምንጭና አካባቢዋ የመጡ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን ጎብኝተዋል፡፡