የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል በ2010 ዓ/ም ለተመረቁ 240 የአካውንቲንግና ፋይናንስ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች /IFRS/ ላይ ከሰኔ 25-29/2010 ዓ/ም ድረስ ለተከታታይ 5 ቀናት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ የትምህርት ክፍሉ መ/ራን ወቅቱ የሚፈልገውን የIFRS ግንዛቤ አግኝተው ለተማሪዎች ተደራሽ በማድረግ የሪፖርት አቀራረብ ዘዴው የተቀላጠፈ፣ ዘመናዊና ከሁሉም ጋር የሚያግባባ እንዲሆን የበኩላቸውን ጉልህ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ስለሆነም ተመራቂዎቹ ለስልጠናው ልዩ ትኩረት በመስጠት የተሻለ ግንዛቤ ጨብጠው በስራው ዓለም ተፎካካሪ እንዲሆኑ፣ ወደ ህብረተሰቡ ዘልቀው ያገኙትን ዕውቀት ለሌላው እንዲያስተላለፉና በተግባር ላይ እንዲያውሉት አሳስበዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ልሳነወርቅ አማረ እንደገለፁት IFRS በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ሲሆን ኢትዮጵያ በአዋጅ ቁጥር 847/2007 ዓ/ም ተቀብላ በመተግበር ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም ተመራቂ ተማሪዎች በዓለም እና በሀገር አቀፍ ገበያ ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ብሎም ለአካውንቲንግና ፋይናንስ ሪፖርት አፈፃፀምና አተገባበር አመቺ እንዲሆን የIFRS ስልጠናን መውሰድ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም የትምህርት ክፍሉ መ/ራን ስልጠናውን ወደ ተማሪዎች በማውረድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

መ/ር ልሳነወርቅ አክለውም በIFRS የሚቀርብ የፋይናንስ ሪፖርት ማንኛውም ዜጋ ሊረዳው የሚችለውና ከሌሎች የውጪ ሀገራት የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ የሂሳብ ሪፖርቱ እውነትን መሰረት ያደረገና የህብረተሰቡን ጥቅም የሚያስከብር እንዲሁም መንግስት የሚገባውን ግብር እንዲሰበስብ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በስልጠናው ከዚህ ቀደም የነበረው ዓለም አቀፍ የአካውንቲንግ ደረጃዎች /IAS 41/  እና በአሁኑ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች /IFRS/ መካከል ያለው አንድነትና ልዩነት በስፋት ተቃኝቷል፡፡ በዚህም IFRS ሙሉ ለሙሉ የቀድሞውን ስርዓት የሚያፈርስ ሳይሆን IAS 41ን ጠቅልሎ የሚይዝና የአካውንቲንግን ሂሳብ አሰራር መርህን የሚቆጣጠር እንደሆነ በስልጠናው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ፣ የሰራተኛ ጥቅማ ጥቅሞች በIFRS፣ የግብር አከፋፈል ስርዓት እና የአግሪካልቸራል ቢዝነስ የመሳሰሉት በስልጠናው  ተዳሰዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ለግልና የመንግሥት ድርጅቶች አዲሱን ‹‹የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ደረጃዎች›› ስልጠና እንዲሰጥ በተጣለበት ኃላፊነት መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ ለ2010 ዓ/ም የአካውንቲንግና ፋይናንስ ተመራቂ ተማሪዎች ስልጠናውን የሰጠ ሲሆን ስልጠናው ተመራቂ ተማሪዎች በዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ገበያ ብቁና ተፎካካሪ እንዲሁም ተመራጭ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ የአሠራር ሂደት መከተል ውጤታማ ስለሚያደርግ ስልጠናውን ወደ ተግባር መቀየር ይገባል ብለዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ቀደም ሲል በስርዓተ ትምህርቱ ያልተካተቱ በርካታ አዳዲስ ደረጃዎችን እንዲያውቁ የረዳቸው መሆኑን ገልፀው  ወደ ስራ ዓለም ሲቀላቀሉ IFRS አዲስ እንዳይሆንባቸውና ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱት የትምህርት ክፍሉ  መ/ራን አድናቆታቸውን ችረዋል፡፡ በተጨማሪም  ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት ስልጠናውን እንዲያገኙ ዕድሉን ያመቻቸላቸውን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲንና የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍልን አመስግነዋል፡፡