በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል የጌዴኦ ዞን ህዝቦች መካከል በቅርቡ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል፡፡  በመሆኑም ከዩኒቨርሲቲው  400 ፍራሾችና 2000 የመመገቢያ ሳህኖች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተሰበሰቡ  የተለያዩ አልባሳትና ጫማዎች ድጋፍ ሐምሌ 22/2010 ዓ/ም ለተፈናቃዮቹ ተሰጥቷል፡፡

‹‹የተፈናቃዮቹ ችግር መንስኤ የህዝብ ለህዝብ መፈላለግ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል ›› ያሉት በጌዴኦ ዞን የደ/ኢ/ህ/ዴ/ን ን/ቅ/ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት አደረጃጀት ዘርፍ ም/ኃላፊ አቶ ተካልኝ ተስፋዬ እንደገለፁት የመልካም አስተዳደር እጦትና የጥገኛ ኃይሎች ሴራ የችግሩ መነሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡ምስሉን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የጌዲዮ ዞን ደ/ኢ/ህ/ዴ/ን ን/ቅ/ጽ/ቤት ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የወቅቱ የተፈናቃዮች አልባሳትና ቁሳቁሶች ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ደመላሽ ብሬ ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ድጋፍ ወገናዊነቱን ያስመሰከረ እንዲሁም መደመርን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ያሳየ በመሆኑ ለቀጣዩም ቢሆን በማናቸውም ህብረተሰባዊ ጉዳዮች ተሳትፎ ላይ ይህንን በጎ ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ደመላሽ ገለፃ በፌዴራል መንግስት በኩል የእርቀ ሠላም ኮሚቴ በማቋቋም እንዲሁም ከሃይማኖት መሪዎችና ሀገር ሽማግሌዎች ጋር የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ተፈናቃዮች በቅርብ ጊዜ ወደ መጡበት ቀያቸው ለማስመለስ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

‹‹ተረስተን የምንቀር መስሎኝ ነበር ነገር ግን ህዝቡ ደረሰልን ›› በማለት በደስታ ስሜት ሃሳቡን የገለፀው ተፈናቃይ ወጣት መስከረም ስንታየሁ  ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ብሏል፡፡

ቁሳቁሶቹን ባስረከቡ የዩኒቨርሲቲው ቡድን አካላት የተጎበኘውን በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የሚገኘውን የማኑፋክቸሪንግ ክላስተር መጠለያ ጣቢያን ጨምሮ ባሉት 77 መጠለያ ጣቢያዎች ከ860 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡