አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2011 የትምህርት ዘመን 1 የመጀመሪያ፣ 6 የሁለተኛ እና 8 የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመክፈት የውስጥና የውጪ ሥርዓተ-ትምህርት ግምገማዎችን በማካሄድ  አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የህዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ ሥራ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ቨተርነሪ ኤፒዲሞሎጂ፣ እጽዋት እርባታ፣ እንስሳትና ወተት ተዋጽኦ ሣይንስና ቴክኖሎጂ፣ ሎጅስቲክስና ሳፕላይ ቼይን ማኔጅመንት፣ ሥነ-ህንፃ፣ ሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን ለዘላቂ ልማት የማስተርስ ዲግሪ እንዲሁም የጂኦኢንፎርማቲክስና ምድር ምልከታ ለሥነ-ውኃ ጥናት፣ የውኃ እና አካባቢ ምህንድስና፣ የውኃ ሀብት ምህንድስና፣ የከርሰ ምድር ውኃ ምህንድስና፣ አፈርና ውኃ አጠቃቀም፣ ሆርቲካልቸር፣ የእንስሳት ምርታማነት እና ኮምፒዩቲንግና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት የሚጀመርባቸው  አዳዲስ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እንደገለፁት እንደ ነባር ዩኒቨርሲቲ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ ዕቅድና ተልዕኮ በመሆኑ የፕሮግራሞቹ መከፈት ዩኒቨርሲቲውን አገራዊ ተልዕኮ ከማሳካትና ከዩኒቨርሲቲው ዕቅድ አንፃር እንደ ትልቅ ስኬት የሚታዩና ሀገራዊ ፋይዳቸውም የጎላ ነው፡፡

በተወሰኑት አዳዲስ ፕሮግራሞች ከትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች ተመድበው ምዘገባ የተጀመረ መሆኑን የተናገሩት ም/ፕሬዝደንቱ ፕሮግራሞቹን ለማስጀመር ዝግጅቱ ከሞላ ጎደል የተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የሰው ኃይል ከማሟላት አኳያ የመምህራን ቅጥር እየተፈፀመ ሲሆን የቤተ-መጽሐፍትና የቤተ-ሙከራ ግብአቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ፕሮግራሞቹን ለማስጀመር በተለይ በተፈጥሮ ሣይንስ መስክ ያሉት ቤተ-ሙከራዎችና ቤተ-መፅሐፍት ያላቸው ግብአትና አደረጃጀት በቂ መሆኑን አስረድተው የጥራት ጉዳይ የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ ትኩረት በመሆኑ አስፈላጊ ግብአቶች እንዲሟሉ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

ም/ፕሬዝደንቱ ሥርዓተ ትምህርቶቹ ከመዘጋጀታቸው አስቀድሞ ያላቸው ሀገራዊ ፋይዳና ጠቀሜታ እንዲሁም የገበያ ላይ ተፈላጊነት በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን ገልፀው በተለይ መንግሥት የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ለማብቃትና የትምህርት ዝግጅታቸውን ለማሳደግ ለሚያረገው ጥረት በእነዚህ የትምህርት መስኮች ተመርቀው የሚወጡ መ/ራን ክፍተቱን በመሸፈን ረገድ  ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ2010 የትምህርት ዘመን በ61 የትምህርት ክፍሎች በ74 የቅድመ ምረቃ እንዲሁም በ83 የ2ኛ ዲግሪና በ13 የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ35 ሺ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በርቀትና በተከታታይ ትምህርት ሲያስተምር መቆየቱ ይታወቃል፡፡