የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በ2011 በጀት ዓመት ከአጋር ኢንደስትሪዎች ጋር ትስስሩን በማጠናከር በቴክኖሎጂ የታገዙ፣ የፈጠራ ክህሎታቸውን በተግባር የሚያሳዩና የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ብቁና ተወዳዳሪ ምሁራንን ለማፍራት የበኩሉን እንደሚወጣ ገለፀ፡፡ 

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለፁት ከአጋር ኢንደስትሪዎች ጋር የተሻለ ትስስር መፍጠሩ በኢንደስትሪዎች የሚመረቱ ምርቶች በቴክኖሎጂ ዕውቀት የታገዙ እንዲሆኑ ከማስቻሉ ባሻገር ከመንግስት ሥራ ጠባቂነት አስተሳሰብ የፀዱና የሥራ ፈጠራ ባህልን ያዳበሩ ምሁራንን ለመገንባት እንዲሁም ኢንደስትሪዎች ጥሩ የምርምር መዳረሻ እንዲሆኑ ለማስቻል ሚናው የጎላ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከመፈጠሩ በፊት ኢንደስትሪዎች በሚያመርቷቸው ምርቶች ጥራትና የገበያ ፍላጎት ላይ ሰፊ ክፍተቶች ከመፍጠሩም ባሻገር አገሪቱ በዘርፉ ተወዳዳሪ እንዳትሆን አድርጓት ነበር ያሉት ዶ/ር ቶሌራ  ትስስር ከተፈጠረ ወዲህ  ጥሩ መነቃቃቶች እየታዩ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዳይሬክቶሬቱ በ2010 በጀት ዓመት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የዩኒቨርሲቲው አጎራባች ከሆኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር ወርሃዊ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ማዘጋጀትና የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ በዩኒቨርሲቲው ጊዜያዊ የICT እና የቴክኖሎጂ ማዕከል ማቋቋም እንዲሁም ዩኒቨርሲቲውን የኬሚስትሪ፣ የአፈር ሣይንስ፣ የሚትዮሮሎጂ እና መሠል ምሁራንን በኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት በማሳተፍ የፕሮጀክቱን የምርት ችግሮችና ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሄ  ሃሳቦችን የሚገልፅ  ፕሮፖዛል ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባፈራቸው ዘመናዊ  የወተት መናጫ አጠቃቀምና ምርታማነት ላይ በቦንኬ፣ ካምባ፣ ደምባ ጎፋ እና ዛላ ወረዳዎች ለሚገኙ  እንስት አርብቶና አርሶ አደሮች ሥልጠና መስጠት፣ ከኬሚካል፣ ከምግብ፣ ከብረታ ብረትና ከጨርቃ ጨርቅ ኢንደስትሪዎች ጋር የመግባቢያ ሠነድ መፈራረም፣ ምርምሮችን መሥራት እንዲሁም የአገር ሀብት የሆኑ የቴክኖሎጂና የኮምፒውተር  ዕውቀቶች፣ ሃሳቦችና የሥራ ፈጠራ ውጤቶች  በተገቢው ሁኔታ የሚደራጁበት እና የቴክኖሎጂ ሥልጠናዎች የሚሠጡበት ቋሚ የኢንኩቤሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል ማቋቋም ዳይሬክቶሬቱ በ2011 በጀት ዓመት ለማከናወን  ካቀዳቸው ዕቅዶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ዳይሬክቶሬቱ በአንድ ዙር 4 እንጀራ በ45 ሰከንድ ውስጥ መጋገር የሚችል ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ፣ ዘመናዊ የመማሪያ ሠሌዳ እና ዘመናዊ የወተት መናጫ ፈጥሮ በማላመድ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ለማሸጋገር እንዲሁም የህብረተሰቡን ፍላጎት በመለየት ተጨማሪ 3 የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት