ዩኒቨርሲቲው የ2011 በጀት ዓመት የመማር ማስተማር ሂደት ሠላማዊ እንዲሆን በጋራ መሥራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ከዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና ተማሪ ተወካዮች፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት፣ ከዞኑ መንግሥት ኃላፊዎች፣ ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከኃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 06/2011 ዓ/ም የትስስር ፎረም ውይይት አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት የውይይቱ ዓላማ አገሪቱ ካለችበት የለውጥ ጎዳና ጋር ተያይዞ በየአካባቢው በሚከሰቱ ግጭቶች መነሻነት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ስጋቶችን ማስቀረት፣ በ2011 በጀት ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ያለ አንዳች ስጋት መቀበል እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው መማር ማስተማር ዙሪያ ችግር የሚፈጥሩ የዩኒቨርሲቲው እና የአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያዋ ተግዳሮቶች ላይ ውይይት በማድረግ የጠራ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የአገር አንድነትን ማጠናከር፣ ‹‹የእብድ ቀን›› እና መሰል በተማሪዎች የሚከናወኑ አላስፈላጊ ባዕድ ፕሮግራሞችን ማስቀረት፣  በዩኒቨርሲቲው ውስጥና አካባቢ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ማስወገድ፣ በዩኒቨርሲቲው ዙሪያ የሚሠሩ የንግድ ድርጅቶች  አደንዛዥ ዕፅ እንዳያዘዋውሩ መከላከል እንዲሁም ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል፣ የእምነትና ብሄር ግጭቶችን መከላከል እና መሰል  ጉዳዮች የውይይቱ  የትኩረት ነጥቦች ነበሩ፡፡

በውይይቱ እንደተገለፀው ባለፉት የትምህርት ዘመናት ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የተጠናከረ ውይይት በማካሄድ የሚፈጠሩ ችግሮችን ቀድሞ በማምከን የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ የአርባ ምንጭ ከተማን ሠላም ለማስጠበቅ  እንዲሁም የሚከሰቱ ጥቃቅን ክፍተቶች ወደ ግጭቶች እንዳያመሩ ሠፊ ሥራዎች ሠርቷል፡፡

ሠላምን ከማስጠበቅ ጋር ተያይዞ ያለን ቁርጠኝነት ደካማ መሆን ችግር ላይ እንድንወድቅ ከማድረጉም ባሻገር መስዋዕትነት አስከፍሎናል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች የዩኒቨርሲቲውን ብቁ የሀገር ተረካቢ ዜጎች የማፍራት ዓላማና ተግባር በመደገፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል፡፡ የስጋት መነሻ የሆኑ ችግሮችን በመለየት ሠላምን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት አለብንም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲያችን የ2011 ትምህርት ዘመን ሠላማዊና ውጤታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚረዳ ውይይት ከዩኒቨርሲቲው አካባቢ አስተዳደርና ማህበረሰብ ትስስር ፎረም ተወካዮችና ባለድርሻዎች ጋር በጥልቀት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የተቻለ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከተማው ምቹ የመማሪያና መኖሪያ አካባቢ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ ከሀገሪቱ ከሁሉም ማዕዘናት ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የሚመጡ ነባርና አዲስ ተማሪዎችን ከአቀባበል አንስቶ ውጤታማ የትምህርት ዘመን እንዲያሳልፉ እየተሠራም ነው፤ ወደፊትም ይሠራል ሲሉ ተናግራዋል፡፡ እንደ አገርም በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ሥራዎች እየተከናወኑ የሚገኙ መሆኑን በመገንዘብ ከአ/ምንጭ ከተማና አካባቢው ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሄዱ ተማሪዎችን ወላጆች ያለ ስጋት እንዲሸኙ ጭምር ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት