የዩኒቨርሲቲው ሰላም ፎረም ከግንቦት 22-23/2004 .ም በዋናው ግቢ በሰጠው ስልጠና በአምስቱም ግቢዎች የሚገኙ የተማሪዎች የሠላም ፎረም ፕሬዝደንቶችና አባል ተማሪዎች፣ አባል መምህራን፣ የካምፓስ አስተዳደሮች፣ የፀጥታና ደህንነት ሰራተኞች፣ዳይሬክተሮች፣ የጋሞ ጎፋ ዞን ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ተወካዮችና የሃይማኖት መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ስልጠናውን በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት ከዚህ በፊት ከአገልግሎት አሰጣጥና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ግጭቶች ይነሱ እንደነበር በማስታወስ ይህ ፎረም ከተቋቋመ በኋላ ግን በርካታ ችግሮችን በመቅረፍ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከደቡብ ክልል ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ተወክለዉ የመጡት አሰልጣኝ አቶ ኃይሉ ማቲዮስ በበኩላቸው በክልላችን በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ይህ መዋቅር አበረታች እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡አቶ ማቲዮስ አያይዘዉ አደረጃጀቱ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ከመውረዱ በፊት ባለማወቅ ችግር ይፈጥሩ የነበሩ አንዳንድ ተማሪዎች ከጥፋታቸው ሙሉ በሙሉ በመዉጣት የሰላም አምባሳደር እስከ መሆን ደርሰዋል ብለዋል፡፡

የስልጠናዉ ትኩረት አቅጣጫ በዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ የሰላም ባህል እንዲጎለብት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነዉ፡፡በወቅቱ ስለግጭት ምንነት፣መንስኤዎች፣አመላካች ሁኔታዎችና መፍትሄዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች አሰልጣኙ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ወቅት ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ያለዉ የመማር ማስተማር ሥራ አስደሳች መሆኑን በመጥቀስ ለወደፊቱም ሁሉም ተማሪ ለዩኒቨርሲቲዉ ሰላም በጋራ ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል ብለዋል፡፡