በዩኒቨርሲቲው በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጆች አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ 78 ተማሪዎች ሚያዚያ 24/2007 /ም የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ በሽልማት መርሃ ግብሩ ከሁሉም ባቾች ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ 13 ሴት እና 14 ወንድ በድምሩ 27 ተማሪዎች እንዲሁም ከማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ 23 ሴት እና 28 ወንድ በድምሩ 51 ተማሪዎች ተሸልመዋል፡፡

የየኮሌጁ ዲኖች አቶ መስፍን መንዛ እና ዶ/ር ተሾመ ይርጉ እንደገለፁት የሽልማት ፕሮግራሙ ዓላማ በተማሪዎች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ በመፍጠርና ሴት ተማሪዎችን በማበረታታት የትምህርት ጥራትን ማጎልበት ነው፡፡

ከሳይኮሎጂ / ክፍል 3.33 በማምጣት ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ዝግጁ የኔሰው ለትምህርቷ ትኩረት መስጠቷ እና በፕሮግራም መመራቷ ለዚህ ውጤት ያበቃት መሆኑን በመግለጽ ሽልማቱ በቀጣይም ጠንክራ እንድትሠራ መነሳሳት እንደፈጠረባት ተናግራለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው የስርዓተ-ጾታ ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሙኒት መኩሪያ በበኩላቸው ቀደም ባሉት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው የሴት ተማሪዎች ቁጥር ከወንድ ተማሪዎች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ውጤት የሚመረቁ ሴት ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አውስተው የማበረታቻ ሽልማቱ በተማሪዎቹ ላይ በጎ ተፅዕኖን የሚሳድር ነው ብለዋል፡፡

ለተማሪዎቹ የተዘጋጀውን ሽልማት የሰጡት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት / አጌና አንጁሎ ፕሮግራሙ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡና መምህራን ተማሪዎቻቸው ያሉበትን ደረጃ እንዲያውቁ የሚረዳቸው በመሆኑ በቀጣይም በሌሎች የዩኒቨርሲቲው ኮሌጆች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡