የዩኒቨርሲቲው ህግ ት/ቤት በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙ ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ለተወጣጡ 30 ዳኞች በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት እና በደ//// ክልላዊ መንግስት ህጎች ዙሪያ ያላቸውን የህግ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ የሚረዳ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ካወቃቀራቸውና ለህብረተሰቡ ካላቸው ቅርበት አንፃር የተፋጠነ ፍትህን በመስጠት እና የፍትህ ተደራሽነት ችግሮችን በመቅረፍ መጠነ ሰፊ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በህግ ት/ቤት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ መምህር ማለፊያ ተሰራ እንደገለጹት የስልጠናው ዓላማ የማህበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞችን የህግ ግንዛቤ በማሳደግ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲያሻሽሉ ማድረግ ነው፡፡ ሥልጠናው በህግ ት/ቤት መምህራን የተሰጠ ሲሆን የሰብዊ መብቶች ምንነት እና ባህሪዎቹ ፣ የቤተሰብ ህጎች ፣ የውርስ ህጎች እና የደ////ክ መንግስት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀትና ማህበራዊ ፍ/ቤቶች በሚሉ አራት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ሥልጠናው የማህበራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በተደራጀና በተቀላጠፈ መልኩ ለመስጠት አንደሚያስችላቸው ከጉርባ ቀበሌ ማህበራዊ ፍርድ ቤት የመጡት ሻንበል ፋንታዬ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡በተመሳሳይ ከድል ፋና ቀበሌ ወ/ሮ ሃዋ ኢብራሂም በበኩላቸው የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን፣ መግለጫዎችን እና አዋጆችን በተመለከተ የተሰጠው ሥልጠና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ በማስተላለፍ ለማህበረሰቡ የሚሰጡት ፍትህ እንዳይዛባ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ የደ///ህ ክልል መንግስት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀትና ማህበራዊ ፍ/ቤቶችን በተመለከተ የጋሞ አከባቢ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መኩሪያ ፈለሃ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጓል፡፡

ዩኒቨርሲቲው መሰል ሥልጠናዎችን ከማዘጋጀት በተጨማሪም በጅንካ እና በሳውላ እንዲሁም በአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ ማዕከሎችን ከፍቶ ተዛማጅ አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ እየሰጠ መሆኑን መምህር ማለፊያ ተናግረዋል ፡፡