በማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ እንዲሁም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጆች አዘጋጅነት ‹‹ምርምር ለልማት›› በሚል መሪ ቃል ከሚያዚያ 30-ግንቦት 1/2007 /ም ለ3ኛ ጊዜ በዋናው ግቢ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የምርምር አውደ ጥናት ላይ ከ15 ዩኒቨርሲቲዎችና ምርምር ተቋማት በተወጣጡ ጥናት አቅራቢዎች 30 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር / ፋንታሁን ወልደሰንበት እንደገለጹት አውደ ጥናቱ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ተመራማሪዎች በወቅታዊ ችግሮች ላይ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንዲጠቁሙ የሚያግዝ ነው፡፡ በተጨማሪም ዓውደ ጥናቱ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የልምድ ልውውጥ በማድረግና የትብብር ምስረታዎችን በማጠናከር ረገድ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ጥናታዊ ጹሑፎቻቸውን ካቀረቡት መካከል በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ሙዑዝ ሃይሉ አንዱ ሲሆኑ የጥናታቸውም ርዕስ ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ጋዜጦች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰጡት ሽፋንየሚል ነው፡፡ መገናኛ ብዙሃን ከሚዲያ መርሆች አንፃር ግድቡን አስመልክቶ እንዴት እደዘገቡት ማወቅን ዓላማ ያደረገው ጥናት በአንዳንድ ጋዜጦች ላይ የሚወጡ ዘገባዎች የናይል ተፋሰስ አገሮችን ጥቅምና ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ ሳይሆኑ በየአገሮቻቸው ፍላጎት ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያም ሆነ ለጎረቤት ሀገሮች ያለው የልማት ጠቃሚነት የጎላ ስለሆነ ሚዲያዎች ሚዛናዊ ሽፋን መስጠት እንደሚገባቸው በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ (አማርኛ) ትምህርት ክፍል መምህርት ህሊና ሰብስበው ‹‹የግጭት አፈታት ሥርዓት ክዋኔ በጌዲኦ ብሄር›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረበች ሲሆን የብሄረሰቡ የግጭት አፈታት ሥርዓት ከማህበረሰቡ መልካም እሴቶች ጋር የተቆራኘ መሆኑን እና የማህበረሰቡን የእርስ በእርስ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ዳስሳለች፡፡ የጥናት አቅራቢዋ በሰጠቸው ተጨማሪ አስተያየት በአውደጥናቱ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች መቅረባቸው ወጣት ተመራማሪዎች ልምድ እንዲቀስሙ ያስችላል ብላለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት / የቻለ ከበደ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ዩኒቨርሲቲው በዋናነት ከሚያሳካቸው አበይት ተልዕኮዎች መካከል ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ ምርምሮች ማካሄድ አንዱ ስለሆነ ተመሳሳይ የምርምር ስራዎች በቀጣይም በሌሎች ኮሌጆች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል፡፡