በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ጋር በመተባበር ለአርባ ምንጭ ከተማ ቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች በደንበኛ አያያዝ ዙሪያ ከግንቦት 25-27/2007 /ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ጥራት ያለው የደንበኞች አገልግሎት ጠቀሜታ እና የደንበኞች ቅሬታ አፈታት ስነ-ዘዴ በስልጠናው ከተዳሰሱ አበይት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይገኛሉ፡፡ የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ት/ት ክፍል ኃላፊ መ/ር ጋሻው ጌታሁን እንደገለፁት ሥልጠናው የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸውን ጥራት ያለውና ቀልጣፋ በማድረግ የድርጅታቸውን ብሎም የከተማውን መልካም ገጽታ ማስተዋወቅ እንዲችሉ የሚረዳ ነው፡፡

ከሰልጣኞቹ መካከል ከፎርቲ ስፕሪንግ ሆቴል የመጣችው ወ/ሪት ራሔል ስዩም ስልጠናው ጥራት ያለው የደንበኞች አገልግሎት ለማጠናከር እንዲሁም ከተገልጋዮች የሚመጡ ቅሬታዎችን በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግራለች፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ጣሰው ጨቾ ዩኒቨርሲቲው የከተማውን የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እየሰጠ ያለው እገዛ የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸው ሠልጣኞችም ከሥልጠናው ያገኙትን እውቀት በተግባር በማዋል ለተጠቃሚዎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡