በዩኒቨርሲቲው የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራርና ከተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተወጣጡ ኃላፊዎች ሰኔ 6/2007 /ም የኤች.አይ./ኤድስ ሜይንስትሪሚንግ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሥልጠናው ዋና ዓላማ በኤች.አይ./ኤድስ ሜይንስትሪሚንግ ላይ ግንዛቤ በማዳበርና ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማሳደግ የጋራ መግባባት ማምጣት መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ዓለሙ ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው ‹‹የኤች.አይ./ኤድስ ስርጭት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት›› በሚል ርዕስ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ በኃይሉ መርደኪዮስ እንዲሁም በሜይንስትሪሚንግ ምንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአቶ አለሙ ጣሚሶ የተዘጋጁ የውይይት ሰነዶች ቀርበው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በቀረቡት የውይይት ሰነዶች መነሻነት ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆኑ በባለሙያዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ መሰል ስልጠናዎችን በየደረጃው ባሉ እርከኖች በመስጠት ግንዛቤውን ማዳበር ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ በዩኒቨርሲቲው በሚገኙ የሥራ ክፍሎች የኤች.አይ./ኤድስ ጉዳይ የዕቅድ አካል ሆኖ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለኤች.አይ./ኤድስ አጋላጭ የሆኑ የኢኮኖሚ ችግሮችን ከመቅረፍ አንጻር ሴት ተማሪዎችንና ሌሎችንም የመደገፍና የመንከባከብ ሥራ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡

በሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን አማካኝነት በተሰጠው በዚህ ሥልጠና የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝደንት ጨምሮ ከ40 የሚበልጡ የበላይ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የሥራና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡