የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን አራተኛ አመትና የግንባታውን መጋመስ በማስመልከት መጋቢት 29/2007 /ም ዩኒቨርሲቲው ዕለቱን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል፡፡

የግድቡ ግንባታ ኃይል ከማመንጨት ዓብይ ዓላማው ባሻገር ተምሳሌታዊ የሆነ ጠቀሜታ ያለውና የአይቻልም መንፈስን ሰብሮ ወደ ይቻላል መንፈስ ያሸጋገረ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ገልፀዋል፡፡ እየተካሄደ ላለው የልማትና የዲሞክራሲ ሂደት በተለይም ለኢንዱስትሪው ሴክተር በቂ ኃይል በማቅረብ ልማታችንን የሚያፋጥን መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ከድህነት ለመውጣት እያሳየ ያለውን ጥረት ለማስቀጠል የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ የተጀመሩ ልማቶችን ከግብ ለማድረስ ሁሉም ዜጋ በቁርጠኝነት መረባረብ አለበት ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ አስገንዝበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጊዜ ጀምሮ የአገራችንን የውሃ ኃብት ለማበልፀግ ታስቦ የተቋቋመ እንደመሆኑ በዘርፉ የሠለጠኑ ምሁራንን ለአገር በማበርከት ግንባር ቀደም ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት እሙን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተቋሙ ሠራተኞች የሁለት ወር ደመወዛቸውን መቶ ፐርሰንት በመክፈል ቦንድ የገዙ ሲሆን ተማሪዎችም ከወር ቀለባቸው በመቀነስ ለግንባታው ስኬት ድጋፍ አድርገዋል፡፡

‹‹አሻራችን ያረፈበት ነውና ኩራት ሊሰማን ይገባል!›› ያሉት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ነገ የተሻለች ሀገር እንድትኖረን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ለግድቡ ግንባታ ካለው ላይ በመቀነስ የሚደያደርገውን ድጋፍ ሳያቋርጥ መቀጠል አለበት በማለት አሳስበዋል፡፡

ፕሮግራሙ በተለያዩ የስነ-ጹሁፍ ስራዎች፣መዝሙሮች፣ስፖርታዊ ውድድሮችና በሌሎች አዝናኝ ትዕይንቶች ደምቆ የተከበረ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣ ተማሪዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡