የሥርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ለ20 የዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራንና ረዳት የቴክኒክ ባለሙያዎች ከግንቦት 7 እስከ 9/2007 /ም በህይወት ክህሎትና አመራር ሰጪነት ሚና ዙሪያ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

በሥነ-ልቦና እና በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህራን የተሰጠው ሥልጠና ዓላማ የመምህራኑን በራስ መተማመን በማጎልበት የችግር ፈችነትና ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው ከፍ እንዲል ማገዝ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የስርዓተ-ፆታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሙኒት መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሴት መምህራን ቁጥርና በኃላፊነት ደረጃ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ ቢሆንም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ያወሱት ዳይሬክተሯ ለዚህም ሴቶች ከተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ተፅዕኖዎች ሙሉ በሙሉ አለመላቀቃቸው እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡

የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል እነዚህን ተጽዕኖዎችንና እንቅፋቶችን በመቅረፍ በራስ መተማመናቸውን እንዲጨምሩና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ዳይሬክተሯ ገልፀዋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር ዘርፍ ሴት ሠራተኞች እንዲሁም ሴት መምህራንና ተማሪዎችን ለመደገፍ እቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ለውጥ ያመጣሉ ተብለው በሚታሰቡ ጉዳዮች ባለሙያዎችን በመጋበዝ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችንና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡