ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ 4400 ተማሪዎችን ባስመረቀበት በዘንድሮው ዓመት ከምረቃው ቀደም ብሎ ሰኔ 17/2007 /ም ለተመራቂዎች የእንኳን አደረሳችሁና የሽኝት ፕሮግራም አከናውኗል፡፡

በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ የትምህርት ዘመኑ በመልካም የመማር-ማስተማር ሂደት የተጠናቀቀና በርካታ መሻሻሎች እንደታየበት ገልጸው ለዚህም የተማሪዎች ድርሻ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሁሉም ዘርፎች መሰል ስኬቶችን ለማስመዝገብ መልካም ጅምሮቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በማውሳት ለእጩ ምሩቃን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር አመራር አካላት ቡድንና የተማሪዎች ተወካይ ቡድን መካከል የተደረገው አዝናኝ የእግር ኳስ ውድድር 3 1 በሆነ ውጤት በአስተዳደር አመራር አካላት ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከአዲስ አበባ በመጡ የሙዚቃ ባንድና ተጋባዥ አርቲስቶችም ዘመናዊና ባህላዊ ሙዚቃዎች ቀርበው ለምሽቱ ልዩ ድምቀት ሆነዋል፡፡

ፕሮግራሙ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት፣ በተማሪዎች ህብረት፣ በተማሪዎች የምረቃ ኮሚቴ እንዲሁም በኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አካላት፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች፣ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች አካላት ታሳታፊ ሆነዋል፡፡