የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር ማስተባበሪያና ኮሜርሻላይዜሽን ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ማላመድና ሽግግር ዙሪያ ከግንቦት 27-28/07 /ም የሁለት ቀናት ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ሥልጠናው ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ ማላመድና ሽግግር እንዲሁም በአእምሯዊ ንብረት አጠባበቅ ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መሆኑን የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደሴ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አእምሯዊ ሀብት ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ ፈቃዱ ኃይሌ በስልጠናው ላይ እንደተናገሩት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በህብረተሰቡ ዘንድ የአእምሯዊ ንብረት እውቀት እንዲዳብርና በቂ የህግ ጥበቃ እንዲያገኝ በመሥራት ላይ ነው፡፡

አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር፣ የማላመድና የማሸጋገር ሥራዎችን በማጠናከር ለማህበረሰቡ ችግር አማራጭ መፍትሄ ለመስጠት በሚቻልበት ሂደትና የፈጠራው ባለቤቶች ከውጤቱ መጠቀም እንዲችሉ እየሰራ መሆኑን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ተረፈ ቤኛ ገልፀዋል፡፡ ይህም በሚኒስቴር መ/ቤቱ ሀገራዊ አቅጣጫዎችን በተከተለ መንገድ ልማቱን የሚያፋጥኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ የማድረግ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኙም ነው አቶ ተረፈ የተናገሩት፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ በስልጠናው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ማላመድና ሽግግር ላይ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ከዚህም ጎን ለጎን በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ላይ የተደራጁና መሰል ሥራዎችን በማከናወን ላይ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን አቅም ከማጎልበት አንጻር የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ግብዓት የሚሆን ስልጠና ለማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር ጉቼ ተናግረዋል ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የማህ/አገ///ቤት ሥር የሚገኘው ቴክኖሎጂ ሽግግርና ኮሜርሻላይዜሽን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከሚሰሩ አዳዲስ የምርምር ሥራዎች ውስጥ ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙትን በመምረጥ፣ በመገምገምና ወደ ተግባር እንዲለወጡ በማበረታታት ተቀባይነት ያገኙትን በኢትዮጵያ አእምሯዊ ሀብት ጽ/ቤት ዕውቅና እንዲሰጣቸው ያመቻቻል፡፡

በሥልጠናው በአርባ ምንጭ ከተማ ከተደራጁ ጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት፣ የፈጠራ ሥራ ባለቤቶችና በዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ መምህራንና ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድና የማሸጋገር ሥራዎችን በትብብር እንደሚሰራ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አለማዬሁ ታዬ ገልፀዋል፡፡