የፌዴራል የስነ -ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአምስቱም ግቢዎች ለሚገኙ ተመራቂ ተማሪዎች ከመጋቢት 21 -25 /2007/ም ድረስ በሙስና ፅንሰ-ሃሳብ ፣ በስነ-ምግባርና በሙስና ወንጀል ህጎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሥልጠናው ዓላማ ተማሪዎቹ ተመርቀው ወደስራ ዓለም በሚቀላቀሉበት ወቅት የተለያዩ ብልሹ አሠራሮች ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ከወዲሁ ግንዛቤ ኖሯቸው ራሳቸውን በስነ-ምግባር በማነፅና ሙስናን በመከላከል የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል እንደሆነ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ሙሉነህ ጉግሳ ገልፀዋል ፡፡

ከኮሚሽኑ የመጡት አቶ ሃረጎት አብረሃም የሙስና ወንጀል ምንነትን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፡-ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ፣ በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ ለመንግስት ሰራተኛ የማይገባ ጥቅም ለመስጠት ቃል የገባ፣ የሰጠ፣ ያቀረበ ወይም ለማቅረብ የተስማማ እንዲሁም በአግባቡ ለተፈፀመ ወይም በአግባቡ ወደፊት ለሚፈፀም የመንግስት ስራ የማይገባ ጥቅምን የሰጠና መሰል ተግባራትን ያከናወነ የሙስና ወንጀል እንደፈፀመ የሚቆጠር መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

በተጨማሪም በስልጣን ያለ አግባብ መገልገል፣ የመንግስት ስራን በማያመች መንገድ መምራት ፣በአደራ የተሰጠን ዕቃ ለሌላ ማዘዝ፣በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ መሰብሰብ ፣ ያለአግባብ ጉዳይን ማጓተት፣ ዋጋ ያለውን ነገር ያለ በቂ ክፍያ ማግኘት፣ ያለአግባብ ፈቃድ መስጠትና ማፅደቅ እንዲሁም ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ መያዝ የመሳሰሉት በመንግሥት ሠራተኞች የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች መሆናቸውን ጠቁመው ተመራቂ ተማሪዎች በቀጣይ ወደ ስራ አለም ሲገቡ ለሙስና ወንጀል እንዳይጋለጡ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል ፡፡

ሠልጣኞቹ በሰጡት አስተያየት ጊዜን በአግባቡ አለመጠቀም ፣ስራ ገበታ ላይ በሰዓት ያለመገኘትና ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ አካሄድ ያለመኖሩ በራሱ ሙስና መሆኑን ተናግረው ስልጠናው በዚህ ሰዓት መሰጠቱ የሙስና ወንጀሎችን ለይተን እንድናውቅና ቅድመ ጥንቃቄ እንድናደርግ የሚያስችለን ነው ብለዋል ፡፡