በዩኒቨርሲቲው የሶስዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል እና በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መ ሴቶች ፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ትብብር የህፃናት ህገ-ወጥ ዝውውርና ጉልበት ብዝበዛ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ከተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የመጡ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሐምሌ 9/2007 ዓ.ም ተካሄደ ፡፡ Click here to see the Pictures.

 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በመክፈቻ ንግግራቸው ህገ -ወጥ የህፃናት ዝውውር በተለይም በጋሞ ጎፋ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች የጎላ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ አሁንም እየተስተዋለ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሶስዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መ/ር ባይሳ ፋዩ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ፅሁፍ ህገ-ወጥ የህፃናት ዝውውር መንስኤዎች፣ የሚያስከትሏቸው ችግሮች፣ የዝውውሩ ተዋንያን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡ የህገ-ወጥ ዝውውር ሰለባ ከሚሆኑት ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶችና እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች እንደሆኑም የውይይት ሰነዱ አመላክቷል፡፡ ይህንን ለማስቆም የተጋላጭነቱን መጠን መቀነስ ፣የወላጆችንና የህፃናቱን ግንዛቤ ማስፋት ፣ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችን ይዞ ለህግ ማቅረብና የመሳሰሉት መፍትሄ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የደ/ብ/ብ/ክ/መ ሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በሀገራችን የህፃናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ መብቶቻቸውን ህገ-መንግስታዊ ከማድረግ አልፎ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችና ድንጋጌዎችን ተቀብሎ በማፅደቅ ተጨባጭ እርምጃ መወሰዱንና አበረታች ለውጥ መታየቱን ገልፀዋል፡፡

የህፃናት ህገ-ወጥ ዝውውርና ጉልበት ብዝበዛን ለመቅረፍ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በተለይም ችግሩ በስፋት በሚስተዋልባቸው በወላይታና በጋሞ ጎፋ ዞኖች ትኩረት በማድረግ ከዞን እስከ ቀበሌ የዘለቀ የንቅናቄ መድረክ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ውጤት እየታየ ቢሆንም በተፈለገው ደረጃ ያልተቀረፈ በመሆኑ ሰፊ ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል ፡፡

ወ/ሮ መሰረት የህፃናት ህገ-ወጥ ዝውውርና ጉልበት ብዝበዛ ማህበራዊ፣ ሥነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል መሆኑን በመገንዘብ ዩኒቨርሲቲው ይህንን የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በማዘጋጀቱ በቢሮው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ችግሩ በበርካታ ወረዳዎች ያለ ቢሆንም በተለይ በአርባ ምንጭ ዙሪያ ቦንኬ፣ከንባ ፣ደራማሎና ጨንቻ ወረዳዎች የከፋ መሆኑን አውስተው በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ በመረባረብ ምንጩን በማድረቅ ህፃናትን ከአስከፊው ስደትና ጉልበት ብዝበዛ ሊታደጓቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡