አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የልማትና የሠላም ሥራዎችን ከከተማ አስተዳደሩና ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችለው ‹የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የአካባቢ አስተዳደርና ማኅበረሰብ ትስስር የሠላም ፎረም› ነሐሴ 08/2007 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ተመሥርቷል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና የአካባቢው ህብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትሥሥር ያላቸው መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ገልፀዋል፡፡ እንደ ፕሬዝደንቱ ገለፃ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በተለይ የአባያና የጫሞ ሐይቆችን ያማከለ የአካባቢ ጥበቃ ፣ የተፋሰስ ልማት፣ የደን ልማትና ጥበቃ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎችንና ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ውጤታማ ለማድረግ በተደራጀ መልኩ መሥራት ተገቢ በመሆኑ ይህ የፎረም መመሥረቻ ውይይት መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አቶ ዮሴፍ ኩማ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በከተማውና በአቅራቢያው በሚገኙ አካባቢዎች የሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች የሚያስመሰግኑ መሆናቸውን ተናግረው በአንፃሩ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጣቸው በመማር ማስተማር እንዲሁም በልማት ሥራዎች ላይ እንቅፋት የሚሆኑ አንዳንድ ችግሮች በመስተዋላቸው ችግሮቹን ለመፍታትና በቀጣይም ከመፈጠራቸው በፊት ለመከላከል ከህብረተሰቡ እና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የተጠናከረ ትሥሥር መፍጠሩ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ለውጥ ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደባልቄ ዳልጮ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሑፍ ዩኒቨርሲቲው በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትነት ከተቋቋመበት ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ አያሌ ኢትዮጵያውያንን በውኃ ምህንድስናው ዘርፍ ማበርከቱን፣ የአካባቢው ህብረተሰብ ከቤቱ ሳይርቅ ዕውቀትና ክህሎቱን እንዲያሳድግ ማድረጉን እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሥሩ 4¸575 ሠራተኞችን አቅፎ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ አስተያየት ሰጪዎች እንዳወሱት ዩኒቨርሲቲው በአቅራቢያቸው መሆኑ ለአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ የሥራ ዕድልን የፈጠረ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተያይዞ ወደ ከተማዋ የሚመጣው የሰው ኃይልም ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ወሳኝ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው፡፡ በመሆኑም የጋራ ተጠቃሚነቱን በማስቀጠል በውስጥም ሆነ በውጭ ለሚፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ህብረተሰቡን ያቀፈ ፎረም መመስረቱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተለይም በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ የሚገኙ የምሽት ክለቦችንና የጫት ቤቶችን የመቆጣጠር ሥራ የከተማ አስተዳደሩንና የነዋሪውን ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ፎረሙ በጋራ የሚሠሩበትን ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲውና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የተማሪ ኅብረት ተወካዮችና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን 16 አስፈፃሚ አካላት ያሉት ፎረም በይፋ ተመሥርቷል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት