በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ሰኔ 27/2007 ዓ.ም በተካሄደው የምዕራብ አባያ የተፈጥሮ ክብካቤና የተፋሰስ ሥራ የባለድርሻ አካላት ወርክሾፕ ላይ የመሬት አስተዳደርን በተሻለ ሳይንሳዊ ቀመር መምራት የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል እንደሚያስችል የሚያሳይ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊ መምህር አቶ አውላቸው ደጀኔ እና የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር መምህር አቶ መስፍን መንታሳ በጋራ ያቀረቡት ጥናት በአካባቢ አየር ለውጥ ምክንያት የሚከሰት የተፈጥሮ አደጋን መከላከል የሚያስችል ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ሳይንሳዊ ቀመርን የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ ቀመር የተፈጥሮ ሃብት አያያዝና አስተዳደር፣ የእንስሳት ሳይንስና የዲጂታል ሳታላይት ካርታ/ጂፒኤስና ጂአይኤስ/ በማቀናጀት የተዘጋጀ ባለ ሙሉ ማዕቀፍ ጥናት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

እንደ መምህር ደጀኔ ገለፃ ጥናቱ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ በከፍተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን ከመኖሪያቸውና ከእርሻቸው ያፈናቀለ የተፈጥሮ አደጋን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ በተለይም በአካባቢው የሚገኘውን የቀመ-ራያ ወንዝ ተከትሎ የሚታየው የግብርና ሥራና የእንስሳት ግጦሽ ለአካባቢው የአየር ንብረት መዛባት መንስኤ መሆኑ በጥናቱ ቀርቧል፡፡

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ታዬ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በምዕራብ ዓባያ ወረዳ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ለማከናወን በቅርቡ ከወረዳው መንግሥት ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ሲሆን ይህ የባለ ድርሻ አካላት ወርክሾፕ የተጀመሩ የውል ስምምነት ሥራዎች ሣይንሳዊ ማዕቀፍ ኖሯቸው እንዲከናወኑ የሚረዳ ነው፡፡

በወርክሾፑ ከታደሙ ባለድርሻ አካላት የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግሥት ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ መሐመድ ኑር ፋሪስ በሰጡት አስተያየት የቀረበው የባለሙያዎች ጥናት የክልሉ መንግሥት ካቀዳቸው የተፈጥሮ ክብካቤና መልሶ ማልማት ሥራዎች ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ ቢሮው ከዩኒቨርሲቲውና ከዞኑ ጋር አብሮ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በወርክሾፑ የምዕራብ ዓባያ ወረዳ አስተዳደርን ጨምሮ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡