በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በጋሞኛ እና በጎፍኛ ትምህርት የቅድመ ምረቃ መርሃ-ግብር ለመክፈት የሚያስችለውን የስርዓተ-ትምህርት ግምገማ ነሐሴ 26/2007 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ Click here to see the Pictures.

 

ግምገማውን በንግግር የከፈቱት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ የትምህርት ክፍሎቹ መከፈት ለቋንቋዎቹ እድገት ከሚያበረክተው የጎላ አስተዋፅዖ ባሻገር  በህገ-መንግስቱ የተቀመጠው የብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ቋንቋ የመጠቀምና የማሳደግ መብት ተግባራዊ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲዉ የሌሎች ብሄረሰቦች ቋንቋዎች ላይ ጥናት በማካሄድ በትምህርት መርሀ-ግብር ለማካተት እንደሚሠራ አስታዉቀዋል፡፡

መምህርት ህሊና ሰብስበው የዳሰሳ ጥናቱን ሲያቀርቡ እንደገለፁት መርሃ-ግብሩን ለመክፈት ከዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ ትምህርት ክፍል የተወጣጡ አራት አባላትን የያዘ የሥርዓተ ትምህርት አዘጋጅ ኮሚቴ በጋሞ ጎፋ ዞን በተመረጡ ስምንት ወረዳዎች ጥናት አድርጓል፡፡

የጋሞኛ ቋንቋ ስርዓተ-ትምህርት ግምገማውን ያካሄዱት የአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህራን ስንታየሁ ሰሙ እና አንጁሎ አዳ ሲሆኑ በተመሳሳይም የጎፍኛ ቋንቋ ስርዓተ-ትምህርትት ግምገማ በኮሌጁ  መምህራን ኡርጋሞ ዚዳ እና ዘሪሁን ሀሊሶ ተካሂዷል፡፡

 

በግምገማው በርካታ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን  በአካባቢ ቋንቋ የመጀመሪያ ድግሪ ፕሮግራም በመክፈት በማስተማር ላይ  ከሚገኙ  ከዋቸሞ፣ ከወላይታ ሶዶና ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ ምሁራን ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደርና ትምህርት መምሪያ ተወካዮችም ለትምህርት ክፍሎቹ መከፈት አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡