‹‹በህዝቦቿ ተሳትፎ ህዳሴዋን ለማረጋገጥ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ እየተጋች ያለች ሀገር ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል 8ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተከብሯል፡፡ Click here to see the Pictures.

በዓሉን በንግግር የከፈተቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ ሃገር የነፃነት፣ የሉዓላዊነት፣ የእኩልነትና የአንድነት መገለጫ በመሆኑ ሁሌም ባንዲራችንን ስንመለከት ነፃነታችንን አስከብረን መቆየታችንንና ለማስከበር የከፈልነውን መስዋእትነት ያስታውሰናል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ በበኩላቸው በአገራችን የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ጭላንጭል በማይታይበትና በቂ መገናኛ ብዙኃንና የመረጃ መለዋወጫ በሌሉበት አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሰንደቅ ዓላማቸው ክብርና ፍቅር ሲሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓልን ስናከብር ሰንደቅ ዓላማችን መላው የሃገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፍፁም እኩልነትና በፈቃደኝነት የመሰረቷት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የስኬትና የህዳሴ ጉዞ ማሳያ በመሆኑ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ ዘርይሁን ቦዴ በሰንደቅ ዓላማ ምንነት፣ ከፍ በማድረግ የመስቀል ሥርዓት፣ በሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር እንዲሁም ለሰንደቅ ዓላማ የህግ ጥበቃ ለማድረግ በህገ መንግሥቱ በተካተቱ አንቀፆች ዙሪያ ለበዓሉ ታዳሚዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ምክትል ፕሬዝደንቶች፣ የኮሌጅ ዲኖች እንዲሁም መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ውዝዋዜዎች እና በዩኒቨርሲቲው ፀጥታና ደህንነት ክፍል ባልደረቦች ወታደራዊ ሰልፍ ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በመዘመር ሰንደቅ ዓላማ የመስቀል ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት