በኢፌዴሪ የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99 እና አዋጁን ለማስፈፀም በወጡት ደንቦችና መመሪያዎች እንዲሁም የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰንን አስመልክቶ ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ጋር በመተባበር ለሰው ኃብት ልማት ዳይሬክቶሬት ሠራተኞች፣ ለሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች ጳጉሜ 2/2007 ዓ.ም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲዉ የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ ሥልጠናው በተለያዩ የአስተዳደር ጉዳዮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ በመሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የአዋጁ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላቸውን ዝርዝር አፈፃፀም፣ መብትና ግዴታ እንዲያዉቁ ይረዳል ብለዋል፡፡

በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ውብሸት የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99 አስመልክተው ባቀረቡት ማብራሪያ የሰው ኃብት ሥራ አመራር ተግባራት፣ የሜሪት ሥርዓት መግለጫዎች፣ መሠረታዊ የሲቪል ሰርቪስ ሕጎች ፣ የቅጥር፣ የደረጃ ዕድገትና የዝዉዉር መመሪያዎች ዝርዝር የአፈጻፀም ሂደት ተካተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ  በታህሳስ ወር 2008 ዓ.ም ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን አዲስ የሥራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን ትንተና ያቀረቡት አቶ መብራቱ ካሳዬ አዲሱን የስራ ምዘና ፅንሰ ሐሳብ፣ አስፈላጊነት፣የደረጃ አወሳሰን ሂደትና ዘዴዎች አስመልክተው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አዲሱ የሥራ ምዘና ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ በሚል መርህ ፍትሐዊነትን በማስፈን ግልፅና ተገቢ የሆነ አንፃራዊ የሥራዎች ደረጃና የደመወዝ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑ በማብራሪያው ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት አማካሪ አቶ ማሌቦ ማንቻ ሥልጠናው ሲሠራበት የቆየውን የመመሪያዎችና የደንቦች  አተገባበር ክፍተቶችን ያሟላና የአዲሱን የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ አፈጻጸም ግንዛቤን አስቀድሞ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ አቶ ማሌቦ አክለውም ከተለያዩ የስራ ክፍሎች የመጡ ተሳታፊዎች የሥልጠናውን ግብዓት ወደ ሥራ በመተርጎም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

በሥልጠናው የሰው ኃብት ልማት ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎች፣ የሁሉም የሥራ ክፍል ዳይሬክተሮችና የቡድን መሪዎች በአጠቃላይ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡