አካዳሚው ከሚያከናውናቸው አበይት ተግባራት መካከል የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስፖርት ፌስቲቫል መሳተፍ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መገንባትና ማደስ፣ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠትና ዓመታዊ የጥናትና ምርምር አውደ ጥናት ማካሄድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአካዳሚው ዳይሬክተር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው እንደገለፁት በ2008 በጀት ዓመት በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል ዩኒቨርሲቲውን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመመልመል የሚያስችል የውስጥ ውድድር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በየካምፓሱ በሚደረጉ የተለያዩ ውድድሮች ዲፓርትመንቶች ለካምፓስ ዋንጫ የሚፎካከሩ ሲሆን በውድድሩ የተሻለ ብቃት ያላቸው ስፖርተኞች ዩኒቨርሲቲውን በመወከል በስፖርት ፌስቲቫሉ ይሳተፋሉ፡፡ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የባህል ስፖርትን ጨምሮ በ13 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራል፡፡
አካዳሚው የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በመገንባትና በማደስ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ በነጭ ሳርና በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ካምፓሶች የጂምናዚየም አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በቅርቡ የውሃ ዋና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡  በሌሎች ካምፓሶችም ተጨማሪ ጂምናዚየሞች እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡
አካዳሚው ለስፖርተኞችና በዞኑ ለሚገኙ የስፖርት ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ለመስጠትም አቅዷል፡፡ በዚህም መሠረት ለተመረጡ ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ለ30 ወንድና ለ30 ሴት ታዳጊ ሕፃናት የእግር ኳስ እንዲሁም ለተመረጡ ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ 10 ወጣቶች የአትሌቲክስ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ለስፖርት ሳይንስ ተማሪዎች በተመረጡ የሙያ ዘርፎች ባለሙያዎችን ከውጪ በመጋበዝ ተጨማሪ ዕውቀት የሚያገኙበት ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን በእግር ኳስ ዳኝነትና አሰልጣኝነት ከ5ቱም ካምፓሶችና ከአካባቢው የሚመረጡ ተማሪዎች ስልጠና ያገኛሉ፡፡ የቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር ለመፍጠር ዓመታዊ የጥናትና ምርምር አውደ ጥናት ማካሄድም በዕቅዱ ተካቷል፡፡