2008 /ም ዩኒቨርሲቲውን ለተቀላቀሉ 5700 አዲስ ገቢ ተማሪዎች ጥቅምት 28/2008 /ም የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካሂዷል ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በመክፈቻ ንግግራቸው ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ዩኒቨርሲቲያችንን ምርጫ አድርጋችሁ የተቀላቀላችሁን ውድ ተማሪዎቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማርና የምርምር ሥራዎች እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎቶች ተማሪዎች ቀጥተኛ ተሳታፊዎች በመሆንና ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት ለውጤት እንዲበቁ አሳስበዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ አክለዉም ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲዉ የሚኖራቸዉ ቆይታ መልካም እንዲሆንላቸዉ ተመኝተዋል ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ በቀለ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የሚኖራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸዉን አገልግሎቶች ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በጥራት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ተማሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ዝግጅቱ ስለ ዩኒቨርሲቲዉ አገልግሎት አሰጣጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንዲረዱ ያገዛቸው ከመሆኑም በተጨማሪ የእንግድነት ስሜት እንዳይፈጠርባቸዉም ያደረጋቸዉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘዉም እንዲህ አይነት ደማቅ የእንኳን ደህና መጣችሁ ዝግጅት መደረጉ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ያለዉን ክብር የሚያሳይና በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው ለሚኖራቸው ቆይታ ብሩህ ተስፋን የሚፈነጥቅ ነው ብለዋል፡፡

በዝግጅቱ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ሙዚቃና ዉዝዋዜዎች በማቅረብ ለፕሮግራሙ ድምቀት ሰጥቷል፡፡