ዩኒቨርሲቲው 16 ሚሊየን ብር በሚሆን ወጪ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ማሻሻያ ፕሮጀክት ለከተማው ውኃ አገልግሎት ድርጅት ያስረከበ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ የአገልግሎት አቅርቦትና አጠቃቀም የጋራ መግባቢያ ስምምነት ሰነድ በ12/04/08 ዓ.ም ተፈራርሟል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ለከተማው ህብረተሰብ የሚቀርበውን የውሃ አገልግሎት በጋራ ሲጠቀም የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በከተማው የተለያዩ ክፍሎች ተጨማሪ አራት ግቢዎች በመገንባታቸውና የተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በተፈለገው መጠን አቅርቦትንና ፍላጎትን ማጣጣም አልተቻለም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍና በተጓዳኝም የከተማውን ነባር የውኃ አቅርቦት አቅም ለማሳደግ በ2006 ዓ.ም ተጨማሪ የውሃ ፓምፕ ተከላና የመስመር ዝርጋታ ስራ አከናውኗል፡፡
የአርባ ምንጭ ውኃ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ አብርሃም እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በሰከንድ 60 ሜትር ኪዩብ የነበረውን የውሃ አቅርቦት ወደ 94 ሜትር ኪዩብ አሳድጓል፡፡ በዚህም በቀን 3 ሚሊየን ሊትር ተጨማሪ  ውኃ ወደ ነባሩ የውሃ ቋት በማስገባት የከተማውን የውኃ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ያቃለለ ሆኗል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በውኃው መስክ ቀዳሚ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ለአካባቢው ህብረተሰብ ተደራሽ ሥራዎችን በማከናወን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ይህ ፕሮጀክትም ነዋሪዎች እንዲሁም የከተማውን ህዝብ 1/5ኛ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች ካልሆነ በቀር የውሃ መቋረጥ ችግር እንዳይገጥማቸው የሚያደርግ ነው፡፡
በከተማው ክልል የሚገኙ የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች በዘላቂና አስተማማኝ ደረጃ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚያገኙበት ሥርዓት እና ከአቅርቦቱ ጋር ተያይዞ ችግሮች ሲገጥሙ በቅንጅት መፍትሔ የሚሰጥበት አሠራር በጋራ መግባቢያ ሰነዱ ተካቷል፡፡


ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት