ዓለም ዓቀፉ የነጭ ሪባን ቀን በዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት እና በሜሪ ጆይ የልማት ማኅበር ጥምረት በ26/03/2008 ዓ.ም በዋናው ግቢ የስኬታማና ታዋቂ ሠዎችን ልምድ በመካፈል ተከብሯል፡፡ Click here to see the Pictures.

የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ መሠለ መርጊያ እንደተናገሩት የነጭ ሪባን ቀን ወንዶች በሴቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ ቃል የሚገቡበትና ጥቃት የሚያደርሱትንም በማውገዝ ከሴቶች ጎን በመቆም አጋርነታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ነው፡፡ በየዓመቱ ከህዳር 16 እስከ 30 ወንዶች ነጭ ሪባን በደረታቸው ላይ በማድረግ ''ጥቃት አላደርስም፤ ሲያደርሱም አይቼ ዝም አልልም፤ ተባባሪም አልሆንም'' የሚል የአጋርነት መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የኃይል ጥቃቶችን የመከላከል ሥራ በተወሰኑ ተቋማት ላይ የሚጣል አይደለም ያሉት አቶ መሠለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲቻል መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  ከህብረተሰቡ  ጋር በቅንጅት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ ከሜሪ ጆይ የልማት ማኅበር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የነጭ ሪባን ክብረ በዓል የቀድሞው የደራሲያን ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው በለጠ፣ የ«ጆይ የኦውቲስቲክ ልጆች ማዕከል» መሥራች ወ/ሮ ዘሚ የኑስ፣ አርቲስት ዮሐንስ ተፈራ (ዳጊ)፣ አርቲስት ካሳሁን ፍስሃ (ማንዴላ)  የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ ራሄል ኤልያስ ለተማሪዎቹ የህይወት ዘመን ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
ዕንግዶቹ ልምዳቸውን ሲያካፍሉ በማንኛውም መስክ ያለንን ኃይል አሟጠን በአግባቡ ከተጠቀምን የማንወጣው ችግርና የማንደርስበት ስኬት አይኖርም ብለዋል፡፡ የትምህርት ዓለም በተለይም ለሴቶች በርካታ  ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩትም  ዓላማን መለየትና ጠንክሮ መሥራት ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በፕሮግራሙ ከሁሉም ካምፓሶች የመጡ ከ500 በላይ ተማሪዎች የታደሙ ሲሆን በግጥም ውድድር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ ተማሪዎች ከዕለቱ የክብር እንግዶች ሽልማቶቻቸውን ተቀብለዋል፡፡
የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ምቹ የትምህርት አካባቢ በመፍጠር ሴት ተማሪዎችን በሁለንተናዊ መስክ ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የማድረግ ዕቅድ ይዞ ይሠራል፡፡ ከሜሪ ጆይ የልማት ማኅበር ጋር በመቀናጀትም ለልጃገረድ ክበብና ለሌሎች አቻ ክበባት አመራሮች፣ ለዩኒቨርሲቲው ነባር እና አዲስ ገቢ ተማሪዎች እንዲሁም  ከአካባቢው ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ ሴት ተማሪዎች የህይወት ክህሎት እና የአመራር ሰጪነት ሥልጠናዎችን ሠጥቷል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት