የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ባካሄዱት የ2008 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በሩብ ዓመቱ የታዩ ጠንካራ አፈፃፀሞች፣ ክፍተቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በሠፊው ተዳሰዋል፡፡ Click here to see the Pictures.

በተማሪ ቅበላ፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በሴቶች ተሣትፎ እንዲሁም በተማሪ መምህር ጥምርታ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ያስቀመጠው 70 በ30 የተማሪዎች ምጣኔን ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉም ከስኬቶቹ አንዱ ነው፡፡
በሩብ ዓመቱ መጽሐፍት፣ የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎች አጋዥ ግብዓቶች ተሟልተው የመማር ማስተማር ሂደቱ በወቅቱ ተጀምሯል፡፡  አዳዲስ ሥርዓተ ትምህርቶችም ተቀርፀው ከትምህርት ሚኒስቴር ህግና ደንብ አንፃር ተፈትሸው ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በእድገትና ትራንፎርሜሽን ዕቅዱ ብሎም በተለያዩ ሀገራዊና ተቋማዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ተካሂደው የጋራ መግባባት መፍጠር ተችሏል፡፡
በማኅበረሰብ አገልግሎት የአጫጭር ጊዜ ስልጠናና የማማከር አገልግሎት እንዲሁም ዩኒቨርስቲው ባቋቋማቸው ስድስት የህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ልዩ የህግ ድጋፍ ለሚሹ ግለሰቦች ከህግ ምክር እስከ ጥብቅና ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በመደበኛ የትምህርት መርሃ-ግብር የመማር እድል ያላገኙ ጎልማሶች በተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ሠልጥነው ለምረቃ በቅተዋል፡፡ በተጨማሪም ከአካባቢው አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ሠፊ የአካባቢ ጥበቃ እና የተፋሰስ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
በአንፃሩ የግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የተማሪ አገልግሎቶችን በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ አለመቻልና የግዥና ፋይናንስ ጉዳዮች መጓተት እንደ ችግር የተነሱ ሲሆን የሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተደረገውን ጥረት አስረድተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደገለጹት ሩብ ዓመቱ የዝግጅት ምዕራፍ እንደመሆኑ ከመምህራንና ተማሪዎች ሥልጠና ጋር ተያይዞ በተፈጠረው የጊዜ ጥበት የተወሰኑ የአፈፃፀም ክፍተቶች ታይተዋል፡፡ ቀጣዩ ሩብ ዓመትም ለክፍተቶቹ የላቀ ትኩረት በመስጠት የተሻለ አፈፃፀም ለማሳየት የምንተጋበት ነው ብለዋል፡፡
በዕቅድ አዘገጃጀትና በመረጃ መረብ ቴክኖሎጂ ካለፉት ጊዜያት የተሻሉ አፈፃፀሞች ቢመዘገቡም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጥቂት ችግሮች የሚታዩ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራበት የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በግምገማው የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት