ዩኒቨርሲቲው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችና የአገልግሎት አሰጣጥ መስፈርቱን እንዲሁም አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ቦታና ደንበኞች አገልግሎት ለማግኘት በቅድሚያ ማሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታ በዝርዝር ለተገልጋዮች ለማሳወቅ የዜጎች ቻርተር አዘጋጅቷል፡፡ የቻርተሩ መዘጋጀት ለዩኒቨርሲቲው ተገልጋዮች የአገልግሎት አሠጣጥ መስፈርት ቅድመ ሁኔታዎችን በግልጽ በማስቀመጥ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሠራር ሂደት በመዘርጋት የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል መሆኑን የስትራቴጂክ ዕቅድ ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ ገልፀዋል፡፡
የቻርተሩ ዓላማ ለተገልጋዮች ቀልጣፋና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት፣ ተጠያቂነትን በግልጽ ማመላከት፣ የተገልጋዮችን መረጃ የማግኘት መብት ማረጋገጥና በዩኒቨርሲቲው አገልግሎት አሠጣጥ ላይ በባለቤትነት አስተያየትና ግብዓት የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ቻርተሩ እንደሚያመለክተው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሠራተኞች፣ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ግብዓት አቅራቢዎች የዩኒቨርሲቲው ተገልጋዮች ናቸው፡፡ ተገልጋዮቹ በመስፈርቱ መሠረት በእኩልነት የመስተናገድ፣ በአካል ጉዳተኝነትና በሌላ ምክንያት ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በልዩ ሁኔታ አገልግሎት የማግኘት እና ቻርተሩ ተጥሶ ሲገኝ ለሚመለከተው የበላይ አመራር አስተያየት ወይም ጥቆማ የመስጠት መብት እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡
ቀጣይ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የአገልግሎት አሠጣጥ መስፈርቱ በየዓመቱ እየተከለሰ ከተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት ግብረ-መልስ የሚሰጥ ሲሆን አገልግሎቱ ደረጃውን የጠበቀና የተገልጋዮችን እርካታ ያስገኘ መሆኑ ክትትልና ግምገማ ይደረግበታል፡፡ በየወቅቱ በሚቀርቡ የክትትልና ግምገማ ሪፖርቶች እና የአገልግሎት ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት በሚሰጡት ግብረ-መልስ መሠረት ቻርተሩ እንደአስፈላጊነቱ በየዓመቱ የእርምትና ማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደና እየተከለሰ ተገልጋዮችና ባለድርሻዎች እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት