11ኛው ሀገር አቀፍ የሥነ -ምግባርና ፀረ ሙስና ቀን “ሕጻናትንና ወጣቶችን በሥነ ምግባር መገንባት ሀገርን መገንባት ነው!!” በሚል መሪ ቃል ታህሳስ 22/2008 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ተከብሯል፡፡
በዓሉ ሲከበር ሀገራዊ መርህን በመያዝ ግንዛቤና ንቅናቄን በመፍጠር መላው የሀገራችን ህዝብ ለፀረ-ሙስና ትግል ራሱን እንዲያዘጋጅ የማድረግ ዓላማን ያነገበ እንደሆነ በዩኒቨርሲቲው የሥነ- ምግባርና ፀረ- ሙስና ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ዮሴፍ ወርቁ ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት በአብዛኛው ተሳታፊ የሆነው ወጣቱ በመሆኑ ወጣቶችን በሥነ ምግባር ማነፅ ሀገር መገንባት ነው፡፡ ፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሥነ-ምግባር የታነፀ፣ የፀረ-ሙስና ወንጀል ምንነትና ቅጣት ላይ በቂ ግንዛቤ ያለው እንዲሆንና ለትግሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ሃላፊነት የመስጠትና ንቅናቄን ለመፍጠር የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ  እንደገለፁት በዩኒቨርሲቲያችን ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረው ይህ በዓል በተለይም ከአራት ዓመታት በፊት የፌዴራሉ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ባዘጋጁት “ሃገር አቀፍ የፀረ-ሙስና ጥምረት ንቅናቄ” ሰነድ መነሻነት የተጀመረ ነው፡፡ በየዓመቱ የጥምረቱን ጉባኤ በማድረግ የተለያዩ የበዓል መልዕክቶችን በማውጣት በተቋማት ንቅናቄ በመፍጠር በተለይም በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ሲከበር ቆይቷል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሌሎች የአገልግሎት መስጫ ሴክተሮች ዜጎች በሥነ-ምግባር የታነጹ፣ ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርና አመለካከት የፀዱ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተለይም በአስተሳሰብ ደረጃ ህጻናትንና ወጣቶችን ከአጸደ ህጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲ ይህንን እሴት ጨብጠውና አጎልብተው ለሀገር ልማት እንዲበቁ ማድረግ በትምህርት ተቋማት  ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡
ዶ/ር ፈለቀ  አክለውም በትምህርት ተቋማት ብዛት ያለው የሰው ኃይል ተሰማርቶ እንዲሁም ከፍተኛ በጀት ተመድቦ የሚሠራ በመሆኑ ትክክለኛ የሀብት አጠቃቀም ስለመኖሩ ከፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ጀምሮ የፌዴራል ኦዲት፣ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር፣ ግዥዎችና ንብረት አስተዳደር ኤጄንሲ ክትትል ያደርጋሉ ብለዋል፡፡በተጨማሪም ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ገንዘብ ማጉደል ወይም የመንግሥትን ሀብት ለግል ጥቅም ማዋል ብቻ ሳይሆን የስራ ሰዓትንም በአግባቡ አለመጠቀም እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በፕሮግራሙ ወቅት በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ባለሙያ በአቶ ላቲኖ ላንጋና የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ወንጀል ምንነትና የወንጀል ቅጣት በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቧል፡፡የፌዴራል  የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ የወንጀል ህግ የተቀመጠውን የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 433 በማሻሻል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 25/2007 የጸደቀው የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 882 አንቀጽ 9 እስከ 33 የተጠቀሱ 23 የሙስና ወንጀል ድንጋጌዎች በቀረበው ሰነድ ተብራርተዋል፡፡ ኮሚሽኑም ይህንን ማስተማር፣ መከላከልና ተጠያቂ ማድረግን በመንግስት መ/ቤት፣ በህዝባዊ ድርጅትና በመንግሥት የልማት ድርጅት ሠራተኞች በመፈፀም ላይ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡ በተሻሻለው የሙስና ወንጀል ህግ መሠረት ዜጎች ሙስና በተከሰተበት አካባቢ ቀጥተኛ፣ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው መረጃ በመያዝ ጥቆማ የማድረግ መብት ያላቸው መሆኑና የጠቋሚዎች ደህንነት ከህግ አንጻር ከለላ ይደረጋል፡፡
ኮሚሽኑ  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተገልጋይ በብዛት ከሚስተናገድባቸው የስራ ክፍሎች መካከል የሰው ሃብት አስተዳደር፣ ግዥና ንብረት አስተዳደር፣ ፋይናንስና በጀት አስተዳደር፣ የተማሪዎች አገልግሎት፣ የደህንነት ክፍል እና  ሬጅስትራር ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡
በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የታደሙ ሲሆን ተሳታፊዎቹ የሀገር እድገት ጸር የሆነውን ሙስና በጋራ ለመከላከል የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣትና የትግሉ አጋር ለመሆን  ቃል ገብተዋል፡፡