የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት አደረጃጀቱን በማሻሻል ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ህብረተሰብ ከአፀደ-ህፃናት እስከ መሰናዶ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለማዳረስ እየሠራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ቤቱን አደረጃጀት በማሻሻል ከአፀደ ህፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በመስጠት ለሰራተኞቹና ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ማድረጉን በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገ/ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ ገልፀዋል:: የት/ቤቱን አቅም የመገንባትና በአገር አቀፍ ደረጃ ምሳሌ የማድረግ ራዕዩን ለማሳካት ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ፕሮግራሞች በመንደፍ የአገልግሎት አድማሱንና ጥራቱን እያሳደገ ይገኛል፡፡
ከዛሬ 16 ዓመት በፊት ለመምህራንና ለአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ልጆች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መስጠት የጀመረው የኮሚዩኒቲ ት/ቤት ቀስ በቀስ ከዩኒቨርሲቲው መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሥሩ ያለው የማህበረሰብ ቁጥር በመጨመሩና በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ልጆቹን በት/ቤቱ የማስተማር ፍላጎት በማሳደጉ የማስፋፊያ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የአፀደ-ህፃናት ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎችና የመመገቢያ አዳራሽ በአዲስ መልክ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃ ሲሆን የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችንም የመማሪያ ክፍሎች ደረጃ ከፍ ለማድረግ በተያዘው የትምህርት ዘመን አገልግሎት መስጠት የሚጀምሩ ባለሦስት ፎቅ ሁለት ህንፃዎች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ግንባታዎቹ በቅርብ ወራት ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
የትምህርት አሰጣጥ ጥራቱን ለማሳደግ የቤተ-መጽሐፍት፣ የቤተ-ሙከራና የትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከላት በመሰራት ላይ ሲሆኑ አጋዥ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍትና የቤተ-ሙከራ ቁሳቁሶች ግዥ በበቂ ሁኔታ የማሟላት ሥራዎች መከናወናቸውን የትምህርት ቤቶቹ ርዕሰ መምህር አቶ ጌታቸው አስፋው ተናግረዋል፡፡ ትምህርት በሥነ-ምግባር የታነፀ መልካም ዜጋን ከመፍጠር አኳያ ድርሻው የጎላ በመሆኑ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ ቀደም ሲል ከአፀደ-ህፃናት እስከ 10ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ደረጃውን በማሻሻል በ2008 ዓ/ም በመሰናዶ 82 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማሩን ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡በትምህርት ቤቱ ከአፀደ-ህፃናት እስከ መሰናዶ ከ870 በላይ ተማሪዎች፣ 37 መምህራንና 14 የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ይገኙበታል፡፡