በ2007 የሥራ ዘመን 3ኛው ሩብ ዓመት የአላቂ ዕቃዎች አጠቃቀም ኦዲት፣ በ2006 በጀት ዓመት ገቢና ወጪ የሆኑ አላቂ ዕቃዎች አመዘጋገብና አጠቃቀም እንዲሁም የፋይናንስና በጀት አፈፃፀም ላይ በማተኮር መስከረም 4/2008 ዓ.ም ግምገማዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የውይይቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲው ከግዥና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ለሚፈጠሩ የአፈፃፀም ችግሮች የጋራ መፍትሄ መፈለግና ውጤታማ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲጎለብት በማድረግ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንደሆነ በዩኒቨርሲቲው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ተረፈች መንግስቱ ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ በግዥና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም በፋይናንስና በጀት በ3ኛው ሩብ ዓመት የተከናወኑ ተግባራት ከመንግስት ደንብና መመሪያ አንጻር  ተፈትሸዋል፡፡ በዚህም በንብረትና በፋይናንስ አጠቃቀም ዙሪያ የውስጥ ኦዲት ሪፖርት መሠረት ተለይተው የቀረቡ ግኝቶች፣ ስጋቶችና የማሻሻያ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
ከታዩ አበይት ችግሮች መካከልም ከግዥ ጋር በተያያዘ ያለውድድር ከአንድ አቅራቢ የተፈፀሙ ግዥዎች፣ ከተቋሙ ዕቅድ ውጭ የተፈፀሙ ግዥዎች፣ በተለያየ መጠን የተሰበሰቡ የዋጋ ማቅረቢያዎች እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የተነሱ ሲሆን ከየኮሌጁና ከኢንስቲትዩቱ የፋይናንስ፣ የግዥና ንብረት ዘርፍ አስተባባሪዎች ጋር ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በቀጣይም ክፍተቶቹን ለመሙላትና ግዥዎችን በእቅድ ለመምራት  በቅንጅት እንደሚሠራ የየዘርፉ አስተባባሪዎችና የሚመለከታቸው የበላይ ኃላፊዎች ገልፀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ፈለቀ ወልደየስ እንደተናገሩት በግዥ አፈፃፀም እና በንብረት አስተዳደር ሂደት ሊከሰት የሚችለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ለመከላከል እንዲሁም ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ አሠራርና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በየበኩላችን የተሰጠንን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ከምንጊዜውም በበለጠ ቅንጅት መስራት ይገባል፡፡
በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የየኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጁና የኢንስቲትዩቱ የፋይናንስ፣ የግዥና ንብረት ዘርፍ አስተባባሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡